ፊንላንድ ከሩሲያ በምትዋሰንበት ድንበር ላይ አጥር መገንባት ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, FINNISH BORDER GUARD
ፊንላንድ ከሩሲያ በምትዋሰንበት ድንበር ላይ "የጸጥታ ሁኔታን ለማጠናከር" ስትል 200 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው አጥር መገንባት ጀመረች።
የአገሪቱ ድንበር ጠባቂ፣ አደገኛ ሽቦ የሚኖረው አጥር የ3 ሜትር ከፍታ ይኖረዋል ብሏል።
ፊንላንድ ከሩሲያ ጋር 1 ሺህ 340 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ድንበር ትጋራለች።
አሁን ላይ የፊንላንድ ድንበሮች በዋናነት የተከለሉት ከእንጨት በተሰሩ አጥሮች ነው።
ፊንላንድ አሁን ላይ ጠንካራ አጥር ለመገንባት የወሰነችው በዩክሬን ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ከግዳጅ ዘመቻ ማምለጥ የሚፈልጉ ሩሲያውያን ቁጥር በመጨመሩ መሆኑን ገልጻለች።
በሰሜን አውሮፓ የምትገኘው ፊንላንድ፣ ምንም እንኳን ሩሲያ ውሳኔዋን አጥብቃ ስትቃወምና ስታስጠነቅቅ ብትቆይም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጥምረትን ለመቀላቀል ተቃርባለች። የፊንላንድ ምክር ቤት አገሪቱ በፍጥነት ኔቶን እንድትቀላቀል የሚያስችል ረቂቅ ላይ መከራከር የጀመረ ሲሆን ረቡዕ ዕለት ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በኢማትራ ድንበር ላይ እየተካሄደ ያለው የአጥር ግንባታዋም በአካባቢው ያለውን ዛፎች በማስወገድ ማክሰኞ ዕለት የተጀመረ ሲሆን፣ የመንገድ ግንባታውንና አጥሩን የማቆም ሥራውን በቅርቡ ለመጀመር እቅድ ተይዟል።
በተወሰነ የአጥሩ ክፍል ላይም በምሽት ማየት የሚያስችሉ ካሜራዎች፣ መብራቶች እና ድምጽ ማጉያዎች ይገጠማሉ ተብሏል።
በኢማትራ ድንበር ላይ የሚገነባው ሦስት ኪሎ ሜትር የሚረዝመው አጥር የሙከራ ፕሮጀክት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ እንደሚጠናቀቅም ድንበር ጠባቂው ተቋም ገልጿል።
አሁን ላይ በድንበሯ ላይ ያሉት የእንጨት አጥሮች በዋናነት ድንበር አልፈው የሚገቡ እንስሳትን ለመከላከል የተሰሩ ሲሆን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ በአገሪቷ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኘውን ድንበሯን ለማጠናከር እየጣረች ነው።
መስከረም ላይ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተጠባባቂ ኃይሎች በዩክሬን እንዲዘምቱ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሩሲያውያን ወደ ፊንላንድ መሰደድ ጀምረዋል።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መክፈቷን ተከትሎ ፊንላንድና ስዊድን ለረጅም ጊዜ ገለልተኛ ሆነው ከቆዩ በኋላ በሚቻለው ፍጥነት ኔቶን ለመቀላቀል ወስነዋል።
አገራቱ ዲፕሎማሲያዊ መሰናክሎች ቢገጥማቸውም፣ የፊንላድ መንግሥት ሚያዝያ ከሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ በፊት ይህንን ማሳካት ይፈልጋል።
እስካሁን ኔቶን ለመቀላቀል ፊንላንድ እና ስዊድን ላቀረቡትን ጥያቄ ድጋፍ ያልሰጡት ቱርክ እና ሃንጋሪ ብቻ ናቸው።












