በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ለምሥራቅ አፍሪካ ምን አንደምታ አለው?

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ሐሙስ ጥር 9/2016 ስብሰባ ጠርቷል።

በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ እንደማትገኝ ተነግሯ።

ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ውጥረት የበለጠ ያባብሰዋል የሚል ስጋት አለ።

የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች፤ ኢትዮጵያ እና ነፃ አገር መሆኗን ያወጀችው ሶማሊላንድ ስለገቡት ስምምነት እና በሱዳን ስላለው የእርስ በርስ ጦርነት ለመምከር ነው ካምፓላ ላይ የተሰበሰቡት።

ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ሶማሊላንድ በኤደን ባሕረ-ሰላጤ 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባሕር በር ኢትዮጵያ ለንግድ እና ለወታደራዊ አገልግሎት እንድትጠቀምበት በኪራይ ልትሰጥ ተስማምታለች።

ኢትዮጵያ ደግሞ ለሶማሊላንድ ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አገር ትሆናለች። አልፎም ከሶማሊያ ነፃነቷን በአውሮፓውያኑ 1991 ያወጀችው ሶማሊላንድ ከኢትዮቴሌኮም አሊያም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የባለቤትነት ድርሻ ታገኛለች።

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች ወይ? የቴሌኮም ወይም የአየር መንገዱ ድርሻ ጉዳይስ? የሚሉት ጥያቄዎች እስካሁን ምላሽ አላገኙም።

ስምምነቱን “የትንኮሳ ተግባር ነው” ያለችው ሶማሊያ ሰነዱ በተፈረመ በነጋው ነው አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ የጠራችው።

ከዚህ በኋላ በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት እየተካረረ እንጂ እየረገበ አልመጣም።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ማሐሙድ ኢትዮጵያን “ጠላት” ብለው የገለጿት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ሰነዱን “ተግባራዊ ለማድረግ” ቃል ገብቷል።

ሶማሊያ ያስቆጣት ኢትዮጵያ ያለፌዴራል መንግሥቱ ፈቃድ የውሃ ክልሏን ልትጠቀም መወሰኗ ብቻ ሳይሆን ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠት የሚለው ሐሳብ ነው።

ሌሎች ምን አለ?

የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአረብ ሊግ እና ዩናይትድ ስቴትስ፤ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንድታከብር ጥሪ አቅርበዋል።

ነገር ግን የሁለቱ አገራት ጎረቤቶች ውጥረቱን ተከትሎ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ ሁኔታውን ማጤን መርጠዋል።

ኤርትራ

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ከመፈረማቸው በፊት ከኤርትራ ጋር የነበራቸው ግንኙነት መሻከሩን የሚያሳዩ ምልክቶች ነበሩ።

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እና የመንግሥት ኃላፊዎች ኢትዮጵያ “ያጣችውን የባሕር በር መልሳ የማግኘት መብት አላት” ሲሉ ለወራት ሲናገሩ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ የሆነችው ኤርትራ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ነፃነቷን ማወጇን ተከትሎ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት የመቀዛዝ ሁኔታን ሲያሳይ፣ በተቃራኒው ሶማሊያ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት እየተሻሻለ መጥቶ ባለፈው ኅዳር የመጀመሪያው የሶማሊያ አምባሳደር በአሥመራ ተሹመዋል።

በተለይ ባለፉት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን ወታደሮች ኤርትራ ውስጥ ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

በተደጋጋሚ ኤርትራን የጎበኙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ማሐሙድ ውጥረቱ መከሰቱን ተከትሎ ወደ አሥመራ አቅንተው ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መክረው ተመልሰዋል።

ነገር ግን የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ውዝግቡን በተመለከተ ኤርትራ ከጎናችን ናት ቢሉም፣ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ውጥረት ጉዳይ እስካሁን በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም።

ጂቡቲ

ጂቡቲ ባለፈው ታኅሣሥ በሶማሊያ እና ሶማሊላንድ መካከል ውይይት እንዲካሄድ ጥረት ስታደርግ ነበር።

እርግጥ ነው ጂቡቲ ከሶማሊያ ጋር ያላት ግንኙነት የጎረበጠ አይደለም። ነገር ግን ከግዙፏ ጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ምጣኔ ሃብት ላይ የተመሠረተ ነው።

ኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነውን የገቢ እና ወጪ ንግዷን የምታሳልጠው የጂቡቲ ወደብን ተጠቅማ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የምትገባው ስምምነት ጂቡቲን ይጎዳል ማለት ነው።

ጂቡቲ ከስምምነቱ አንድ ሳምንት በኋላ ባወጣችው መግለጫ “እንደ ወቅቱ የኢጋድ ሊቀ-መንበርነታችን” ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግጭታቸውን በዲፕሎማሲ እንዲፈቱ እንጠይቃለን ብላለች።

ይህንንም ተከትሎ የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች በአስቸኳይ ካምፓላ ላይ ተገናኝተው ውይይት እንዲያደርጉ ጂቡቲ በጠየቀችው መሠረት ነው የተሰበሰቡት።

ጂቡቲ እንደምትለው ስብሰባውን የጠራችው በሶማሊያ ጥያቄ መሠረት ነው።

ኬንያ እና ኡጋንዳ

ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላት ኬንያ እስካሁን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

ነገር ግን ሶማሊ-ኬንያዊያን ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን ከመውቀስ እና ከመተቸት አልተቆጠቡም።

በአውሮፓውያኑ ጥር 4 በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ያሉ የሕዝብ እንደራሴዎች ናይሮቢ በሚገኘው የኬንያ ፓርላማ ቅጥር ግቢ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርተው የመግባቢያ ሰነዱን አውግዘዋል።

የዳዳብ እንደራሴ የሆኑት ፋራህ ማሊም “ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ግዛት መሬት ለመከራየትም ሆነ የባሕር በር ለማግኘት የሶማሊያ መንግሥትን ይሁንታ ማግኘት አለባት” ብለዋል።

ሌላኛው ምሥራቅ አፍሪካዊት አገር ኡጋንዳም እንዲሁ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

ነገር ግን ባለፈው መስከረም የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ሶማሊላንድ ለመገንጠል የምታደርገውን እርምጃ “ስትራቴጂካዊ ስህተት” ሲሉ ገልጸው፣ በሶማሊያ እና በሶማሊላንድ መካከል ድርድር እንዲደረግ መክረዋል።

ግብፅ

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ያለችው ግብፅ በሰሞኑ ውጥረት ድጋፏን ለሶማሊያ ገልጻለች።

ግብፅ ስምምነቱ ከተፈረመ በቀናት ውስጥ ባወጣችው መግለጫ ስምምቱን “ለቀጣናው ሰላም አደጋ” ስትል የገለጸችው ሲሆን፣ “ከሶማሊያ ጎን ለመቆም” ቃል ገብታለች።

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ለሶማሊያ እና ለኤርትራ ፕሬዝዳንቶች የጉብኝት ግብዣ አቅርበዋል።

ቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል?

ኢትዮጵያ “ሁሉንም ጫና ተቋቁማ” ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ተግባራዊ እንደምታደርግ አሳውቃለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ማኅበራዊ ዕሴቶችን” ጥሰውም ቢሆን የሚቻላቸውን በማድረግ “ኢትዮጵያን ለማዳን” እንዲሚሠሩ ገልጸዋል።

ታኅሣሥ 29/2016 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ጦር አዛዦች ተገናኝተው ስምምነቱን ለማጠናከር ተነጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ወደ ሶማሊላንድ ተጉዘው የበርበራ ወደብን ሊጎበኙ እንደሚችሉ ጭምጭምታዎች ተሰምተው ነበር።

ጥር 05/2016 ዓ.ም. የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲ ባሬ ስምምነቱ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ “ጦርነት ውስጥ ለመግባት” ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቀጥታ ግጭት ይኖራል የሚለው ግምት እምብዛም አይደለም። ምክንያቱም ሁለቱም አገራት በአገር ውስጥ ግጭት እየታመሱ ነው።

ኢትዮጵያ አል-ሸባብ የተሰኘውን ታጣቂ ቡድን ለመዋጋት የተሰማሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ለማስወጣት ልትገደድ ትችላለች።

ታጣቂው ቡድን አል-ሸባብ ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም አደጋ የሆነ ከአል-ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን ነው።

አለመግባባቱ መፈጠሩን ተከትሎ ሶማሊያ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ ተዘግቧል።

ሶማሊያ በኢትዮጵያ የሚገኘውን የሶማሌ ክልል ይገባኛል የሚል ጥያቄ ልታነሳም ትችላለች። ፕሬዝዳንት ማሐሙድ በቅርብ ባሰሙት ንግግር “ሶማሊያ ያጣቻቸው መሬቶች” በማለት ይህን ጠቆም አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ብትሰጥ ሌሎች አገራትም ተከትለው ዕውቅና ሊሰጡ ይችላሉ ወይ የሚለውን ጥያቄ ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።