ታሊባን ዘግቶት የነበረውን የኢንተርኔት አገልግሎት መልሶ አስጀመረ

የታሊባን መንግሥት በመላው አፍጋኒስታን ያቋረጠውን ኢንተርኔት እና የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት መመለሱን ተከትሎ ነዋሪዎች ወደ ጎዳናዎች በመውጣት ደስታቸውን ገለጹ።

በአፍጋኒስታን የሚገኙ ዘጋቢዎች የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች መልሰው መጀመራቸውን ተናግረዋል። የኢንተርኔት መቋረጥን የሚከታተው ኔት ብሎክስ በበኩሉ መረጃዎች የሚያመለክቱት የኔትወርክ ዳታ "በከፊል መመለሱን" እንደሆነ አስታውቋል።

ለአገሪቱ መንግሥት ቅርበት ያላቸውን አንድ ምንጭ ኢንተርኔት እንዲመለስ የተደረገው በታሊባኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ትዕዛዝ መሆኑን ለቢቢሲ አፍጋን ተናግረዋል።

ለ48 ሰዓታት የቆየው የግንኙነት መስመሮች መቋረጥ የንግድ ሥራዎች እና በረራዎች እንዲስተጓጎሉ አድርጓል፤ ነዋሪዎች የአደጋ ጊዜ አገልግሎቶችን የሚያገኙበትን መንገድም ገድቧል።

የአገልግሎት መቋረጡ አክራሪው ኢስላማዊ ቡድን በ2021 ወደ ሥልጣን ከተመለሰ ወዲህ መብታቸው እጅጉን የተሸረሸረባቸው የአፍጋኒስታን ሴቶች ይበልጡኑ እንዲገለሉ ያደርጋል የሚል ፍርሃትም ፈጥሮ ነበር።

ረዕቡ ምሽት ኢንተርኔት መመለሱ እንደተሰማ በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍጋኖች በዋና ከተማዋ ካቡል ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል።

አንድ ነዋሪ፤ "ሁሉም ሰው ደስተኛ ነው፤ [ሰዎች] ስልካቸውን ይዘው ዘመዶቻቸውን እያነጋገሩ ነው" ሲል የነበረውን ሁኔታ ለቢቢሲ አፍጋን ገልጿል።

"አገልግሎት ከተመለሰ በኋላ ከሴቶች እስከ ወንዶች እና የታሊባን አባላት ድረስ ሁሉም ስልክ እያወሩ ነበር። አሁን ከተማው ውስጥ የተሰበሰበው ሰው ብዙ ነው" ሲልም አክሏል።

በኳታር የታሊባን ከፍተኛ ቃል አቀባይ የሆኑት ሱሄል ሻሂን፤ ረዕቡ ከሰዓት ላይ "ሁሉም ግንኙነቶች" መመለሳቸውን ተናግረዋል።

የታሊባን መንግሥት ሁሉን የኔትወርክ ግንኙነቶች እንዲቋረጡ አድርጎ የነበረበትን ምክንያት በተመለከተ እስካሁን ይፋዊ ማብራሪያ አልሰጠም።

ይሁን እንጂ ባለፈው ወር ላይ "መጥፎ ምግባራትን ለመከላከል ሲባል" በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል በሚገኘው ባልክ ግዛት የኢንተርኔት አቅርቦት እንዲቋረጥ መደረጉን የታሊባን ቃል አቀባይ ተናግረው ነበር።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ከተመለሰ ወዲህ በእስላማዊ የሸሪያ ህግ ትርጓሜ መሰረት በርካታ ገደቦችን ጥሏል።

ከ12 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ትምህርት እንዳያገኙ በተከለከለባት አፍጋኒስታን የሚገኙ ሴቶች፤ ኢንተርኔት ከውጪው ዓለም ጋር የሚገናኙበት የሕይወት መስመር መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለሴቶች የሚቀርቡ የሥራ ዕድሎች ላይም ከፍተኛ ገደብ የተቀመጠ ሲሆን፤ ከመስከረም ወር ጀምሮ ደግሞ በሴቶች ተጻፉ መጽሐፍት ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲወገዱ ተደርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት፤ ሰኞ ዕለት በታየው የኢንተርኔት መዘጋት ምክንያት ከቀሪው ዓለም ጋር በመቆራረጡ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከአፍጋኒስታን መውጣቱን አስታውቋል።

ኢንተርኔት መቋረጡ "የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ስጋትን በመደቀን እና በዓለም ላይ ካሉት እጅግ የከፉ የሰብአዊ ቀውሶች አንዱ [የሆነውን የአፍጋኒስታን ሁኔታ] በማባባስ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል" በማለት ስጋቱን ገልጾ ነበር።

የኢንተርኔት በተቋረጠበት ወቅት በመዲናዋ ካቡል ማዕከላዊ ሥፍራዎች የሚገኙ ባንኮች ተዘግተው፣ የገበያ ማዕከላት ባዶ በመሆናቸው እንደዋሉ በዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶችም የተቋረጡ ሲሆን ይህም በውጭ አገራት የሚገኙ አፍጋኒስታናውያን ወደ ቤተሰባቸው የሚልኩት ገንዘብ ወደ አገሪቱ እንዳይገባ አድርጓል።