እስራኤል በወታደራዊ ተቋማቷ ላይ ጥቃት የፈጸመችባት ኢራን እራሷን የመከላከል መብት እንዳላት አስታወቀች

ቴህራን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ተቋማት ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ኢራን ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት አስታወቀች።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱን የፈጸመው ኢራን እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አጋሮቿ የሆኑ ታጣቂ ቡድኖች ለፈጸሙት “ለወራት የዘለቀ ጥቃት” ምላሽ መሆኑን አስታውቋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱን የፈጸመው “በተመረጡ ወታደራዊ ዒላማዎች” ላይ መሆኑን አስታውቆ፣ ኢራን ካለፈው ዓመት መስከረም 23/2016 ዓ.ም. ጀምሮ “ያለማቋረጥ እስራኤል ላይ ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች” ሲል ወንጅሏታል።

ኢራንም ቅዳሜ ንጋት ላይ በዋና ከተማዋ ቴህራን፣ ኹዜስታን እና ኢላም በተባሉ ግዛቶቿ ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ሰፈሮች የእስራኤል ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አስታውቃለች።

የአየር ጥቃቱን ተከትሎ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የእስራኤልን ጥቃት በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የተፈጸመ “ግልጽ ጥሰት” ነው ብሏል።

በተጨማሪም “የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ከውጭ ከሚፈጸምባት የጸብ አጫሪነት ድርጊት ራሷን የመከላከል መብት እና ግዴታ እንዳለባት ታምናለች” በማለት በእስራኤል ለተፈጸመባት ጥቃት ራሷን ለመከላከል ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቃለች

የእስራኤል ወዳጅ የሆኑት አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ግን በአካባቢው ያለው ቀውስ የበለጠ እንዳይባባስ ኢራን የአጸፋ እርምጃ ከመውሰድ እንድትቆጠብ ጠይቀዋል።

ይህ የእስራኤል ጥቃት የተፈጸመው ቴህራን ውስጥ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የሐማስ ፖለቲካ መሪ በመገደላቸው ኢራን ከ200 በላይ ባሌስቲክ ሚሳዔሎችን መስከረም 21/2017 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ከተኮሰች በኋላ ነው።

የእስራኤል አየር ኃይል ሌሊቱን የፈጸመው ጥቃት ኢራን በእስራኤል ላይ የተኮሰቻቸውን ሚሳኤሎች የሚያመርቱ ተቋማትን፣ የአየር ጥቃት መከላከያ እና የሚሳዔል ማስወንጨፊያ ሥርዓቶችን ዒላማ መደረጋቸውን ተገልጿል።

ኢራን በወታደራዊ ይዞታዎቿ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመባት አረጋግጣ፤ “ጥቃቱ ውስን ጉዳት” ቢያደርስም በተሳካ ሁኔታ ማክሸፏን አስታውቃለች።

የኢራን ሠራዊት ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ የኢራን ዜና አገለግሎት በእስራኤል ጥቃት ሁለት ወታደሮች መገደላቸውን ዘግቧል።

በመግለጫው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ሠራዊት “የኢራንን እና የሕዝቧን ደኅንነት እንዲሁም ጥቅም ለመጠበቅ ከወንጀለኛው ጽዮናዊ መንግሥት የተተኮሱ ሚሳዔሎችን ለመመከት በተደረገው ጥረት ሁለት ተዋጊዎቹ መስዋዕትነት ከፍለዋል” ሲል በሰው ላይ የደረሰውን ጉዳት አሳውቋል።

የኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ከጥቃቱ በኋላ ማለዳ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢራን ለፈጸመችባት ጥቃት እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት አላት የምትለው አሜሪካ፣ ነገር ግን በምትውስደው እርምጃ የኢራንን የኑክሌር ማዕከላትን እና የነዳጅ ማምረቻ ተቋማትን ዒላማ እንዳያደርግ አሳስባለች።

በተጨማሪም ለአሁኑ ጥቃት ኢራን የአጸፋ እርምጃ ጥቃት በእስራኤል ላይ እንዳትወስድ አሜሪካ ጠይቃለች። ነገር ግን ኢራን ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ ሌላ ጥቃት የሚያስከትልባት ይሆናል በማለት አንድ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን አስጠንቅቀዋል።

የአሜሪካ ብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ “ኢራን ወደ እስራኤል መስከረም 21 ላስወነጨፈቻቸው ባሌስቲክ ሚሳዔሎች ምላሽ የሚሆን ራስን በመከላከል ተግባር በኢራን የተመረጡ ወታደራዊ ዒላማዎችን መደብደቧን እናውቃለን” ብለዋል።

መስከረም 21 ኢራን ወደ እስራኤል ያስወነጨፈቻቸው ሚሳዔሎች በመከላከያ ኃይሉ መምከናቸው ቢገለጽም ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሚሳዔሎች ግን ማዕከላዊ እና ደቡባዊ እስራኤል ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

ለአሁኑ ጥቃት ምክንያት የሆነው እና ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የፈጸመችው “ሉዓላዊነቷ ተጥሶ” ቴህራን የሐማሱ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ በዋና ከተማዋ ውስጥ በመገደላቸው የአጸፋ እርምጃ መሆኑን አሳውቃ ነበር።

የኢራን ባለሥልጣናት የሐማሱ ፖለቲካ መሪ በኢራን ምድር የተገደሉት በእስራኤል ነው ቢሉም እስራኤል ግን እስካሁን ድረስ ኃላፊነቱን አልወሰደችም።

ኢራን መስከረም 21/2017 ጥቃት ከፈጸመች በኋላ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በምትፈጽመው ጥቃት የሄዝቦላህ መሪ የነበሩት ሐሳን ናስረላህ እና ብርጋዴር ጄነራል አባስ ኒልፎሮውሻን በመገደላቸው የተሰጠ ምላሽ መሆኑንም ጨምራ አስታውቃ ነበር።

በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረቱ የተካረረው የእስራኤል ወታደሮች “የአሸባሪው ሄዝቦላህን ዒላማዎች” ለማስወገድ በሚል ደቡባዊ ሊባኖስን መውረር ከጀመሩ በኋላ ነው።

እስራኤል በኢራን ጥቃት ከጀመረች በኋላ ዋይት ሐውስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መረጃው እንደደረሳቸው እና በቅርበት ሁኔታውን እየተከታተሉት እንደሆነ አስታውቋል።

ይሁን አንጂ የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት በእስራኤል የአየር ጥቃት የአሜሪካ ተሳትፎ እንደሌለበት ተናግረዋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ኢራን በሚያዝያ እና መስከረም ወሮች የፈጸመችው ጥቃት እንዲሁም በቀጠናው ለሚገኙ አጋሮቿ የምታደርገው ድጋፍ “የቀጠናውን መረጋጋት እና ፀጥታ እንዲሁም የዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ አደጋ የጣለ” ሲል ገልጾታል።

የሶሪያ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በበኩሉ የእስራኤል አየር ጥቃት በአገሪቱ ማዕከላዊ እና ደቡባዊ ክፍል የሚገኙ የተወሰኑ ወታደራዊ ካምፖችን ዒላማ መደረጋቸውን ዘግቧል።