የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አገሪቱ ውስጥ በመወለድ የሚገኝ የዜግነት መብት ላይ የተነሳውን ክርክር ሊመለከት ነው

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ፤ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች በአገሪቱ ውስጥ የሚወልዷቸውን ልጆች የአሜሪካ ዜግነትን የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ያላቸው መሆን እና አለመሆኑን በተመለከተ የሚደረገውን ክርክር ሊመለከት ነው።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ወደ ዋይት ሐውስ በገቡ በመጀመሪያው ዕለት፤ ካሳለፏቸው ውሳኔዎች አንዱ አሜሪካ ምድር ላይ በመወለድ የሚገኝ የዜግነት መብትን የሚያግደው ይገኝበታል።

ትራምፕ በዕለቱ በፈረሙት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ ከገቡ ወላጆች አሜሪካ ውስጥ የሚወለዱ ልጆች ዜግነት እንዳያገኙ አድርገዋል። ይሁን እንጂ፤ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ በርካታ የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች ውሳኔው ተፈጻሚ እንዳይሆን አግደዋል።

አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይደረጋል የተባለው ክርክር ገና ቀን አልተቆረጠለትም። በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስም ወራትን ሊፈጅ ይችላል።

ፍርድ ቤቱ የሚያሳልፈው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ትራምፕ በስደተኞች ላይ በከፈቱት ዘመቻ ላይ እንዲሁም አሜሪካዊ ዜጋ መሆን ምን ማለት ነው የሚለው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

የዲፕሎማቶች እና የውጭ አገር ወታደር ልጆች ከሆኑት በስተቀር ማንኛውም አሜሪካ ውስጥ የሚወለድ ሰው የአገሪቱን ዜግነት እንዲያገኝ ያስቻለው 14ተኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የተደረገው ከ160 ዓመታት ገደማ በፊት ነበር።

የሕገ መንግሥት ማሻሻያው፤ "አሜሪካ ውስጥ የተወለዱ ወይም በሕግ የዜግነት መብት ያገኙ እና ለአገሪቱ ሥልጣን የሚገዙ ሰዎች በሙሉ የአሜሪካ ዜጎች ናቸው" በማለት ደንግጓል።

ትራምፕ የፈረሙት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ፤ በሕገ ወጥ መንገድ ወይም በጊዜያዊ ቪዛ ወደ አሜሪካ ከገቡ ሰዎች የሚወለዱ ሕጻናት የዜግነት መብትን እንዳያገኙ ይከለክላል።

ይህ ውሳኔ፤ የትራምፕ አስተዳደር የአገሪቱን የኢሚግሬሽን ስርዓት ለመቀየር እንዲሁም "ለብሔራዊ ደህንነት እና የሕዝብ ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ነው" በማለት የሚገልጸውን የስደተኞች ጉዳይ ለመዋጋት እየወሰዳቸው ካላቸው እርምጃዎች አንዱ ነው።

የትራምፕ አስተዳደር፤ በ14ተኛ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ የተጠቀሰው "ለአገሪቱ ሥልጣን የሚገዙ" የሚለው ሀረግ በጊዜያዊነት ወይም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ ከገቡ ሰዎች የሚወለዱ ልጆችን አያካትትም በማለት ይከራከራል።

የትራምፕን ውሳኔ ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱትን ሰዎች ወክላ የምትከራከረው እና የ 'አሜሪካን ሲቪል ሊብሪቲስ ዩኒየን' ብሔራዊ የሕግ ዳይሬክተር የሆነችው ሴሲሊያ ዋንግ በዚህ አስትማማም።

የሕግ ባለሙያዋ፤ የትኛውም ፕሬዝዳንት 14ተኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በመሠረታዊነት የሰጠውን የዜግነት ቃል ኪዳን መቀየር እንደማይችል በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግራለች።

"አሜሪካ ምድር የሚወለድ ሁሉም ሰው በመወለድ ዜግነት የማግኘቱ ጉዳይ ከ150 ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ሕግ እና ብሔራዊ ባህላችን ሆኖ ቆይቷል" ብላለች።

"በዚህ አግባብ፤ ይህንን ጉዳይ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እልባት ለማሰጠት እንጠብቃለን" ስትል አክላለች።

አሜሪካ፤ በድንበራቸው ውስጥ ለተወለደ ማንኛውም ሰው ዜግነት ከሚሰጡ 30 ገደማ አገራት አንዷ ነች። የትራምፕ ውሳኔን የሚቃወሙ ሰዎች አቤቱታቸውን ካቀረቡ በኋላ በርካታ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች እርምጃ ሕገ መንግሥትን የሚጥስ እንደሆነ ወስነዋል።

በዳኞቹ ውሳኔ ላይ የተነሳውን የይግባኝ አቤቱታ የተመለከቱ ሁለት ፍርድ ቤቶችም በተመሳሳይ የትራምፕ እርምጃ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚደርገውን ውሳኔውን አጽንተዋል።

ይህንን ተከትሎም ትራምፕ ክርክሩን ወደ አገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወስደውታል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፤ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዙ እንዲታገድ የወሰኑት ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ለመመልከት ሥልጣን እንዳልነበራቸው በመግለጽ ብይኑን አስተላልፏል።

ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ ክርክር ያስነሳውን አሜሪካ ውስጥ በመወለድ የሚገኝ የዜግነት መብት ጉዳይ አልተመለከተም።

ከአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ የተደረገው 14ተኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፤ ከዚያ አስቀድሞ በባርነት ስር የነበሩ አሜሪካ ውስጥ የተወለዱ ሰዎችን ጉዳይ በተመለከተ መፍትሔ ለማበጀት የተደረገ ነው።

በፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደርን የወከሉት የሕግ ባለሙያው ዲ ጆን ሳውር በበኩላቸው፤ ማሻሻያው የተደረገው "በጊዜያዊነት አሜሪካን ለመጎብኘት ለሚመጡ ወይም ሕገ ወጥ ለሆኑ የውጭ አገር ሰዎች ልጆች ሳይሆን ነፃ ለወጡ ባሮች እና ለልጆቻቸው ዜግነት ለመስጠት ነው" በማለት ይከራከራሉ።