ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለ40 ዓመታት ያለ ወንጀሉ የታሰረው አሜሪካዊ ከአገር ሊባረር ነው
ባልፈፀመው የግድያ ወንጀል 43 ዓመታት የታሰረው ሱበራማንያም "ሱቡ" ቪዳም አዲስ ማስረጃ ከተገኘ በኋላ በነፃ ቢለቀቅም ዳግም በቁጥጥር ስር ውሏል።
ከአራት አስርት ዓመታት እስር በኋላ ከእስር ሲለቀቅ የቤተሰቦቹ እቅፍ ከመደረሱ በፊት በአሜሪካ የኢምግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማቆያ ጣቢያ እንዲገባ ተደርጓል።
ባለሥልጣኑ ቪዳም ከጨቅላ ሕፃንነቱ በኋላ ወዳልኖረባት ሕንድ ሊያባርረው ጫፍ ላይ ነው።
ጠበቆቹ ትዕዛዙ እንዲቀለበስ እየተፋለሙ ሲሆን፤ ቤተሰቦቹ ደግሞ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከእስር ለማስለቀቅ ቁርጠኛ ናቸው።
እህቱ ሳራሲታ ቪዳም ቤተሰባቸው አዲስ እና እንግዳ የሆነውን መንገድ ለመሻገር እየጣረ መሆኑን ተናግራለች።
ወንድሟ ታራሚዎችን ከሚመክርበት እና የራሱ ክፍል ካለው ማረሚያ ቤት፤ ከሚያውቃቸው ታራሚዎች እና የጥበቃ ሠራተኞች ተነጥሎ ከሌሎች 60 ሰዎች ጋር ወደሚጋራው እና ያሳየው ለውጥ ወደ ማይታወቅበት ማቆያ መዛወሩን ተናግራለች።
በቅፅል ስሙ ሱቡ እየተባለ የሚጠራው ወንድሟ "ስሜ ነፃ ወጥቷል፤ ከዚህ በኋላ ታራሚ አይደለሁም፤ እስረኛ ነኝ" ማለቱን ገልፃለች።
ሱቡ ፍርድ ባገኘበት የግድያ ወንጀል ነፃ ሲወጣ ቤተሰቦቹ ግን ለነፃነቱ አንድ መሰናክል እንዳለው ያውቁ ነበር።
በግድያ ወንጀል እና በዕፅ ጥፋት ብይን ከተጣለበት በኋላ እ.አ.አ በ1988 ከአገር እንዲባረር ትዕዛዝ ተላልፎበት ነበር።
ቤተሰቦቹ የኢምግሬሽን መዝገቡን ለመክፈት ወጥነው የነበረ ቢሆንም፤ የመዝገቡ ሁኔታ አሁን ሌላ እንደሆነ መረዳታቸውን እህቱ ተናግራለች።
የአሜሪካ የኢምግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለቢቢሲ የአስተያየት ጥያቄ ምላሽ ባይሰጥም ለሌሎች መገናኛ ብዙኸን ሱበራማንያም ቪዳም ከአገር እስኪባረር ድረስ በቁጥጥር ስር እንደሚቆይ ተናግሯል።
ቤተሰቡ ያለወንጀሉ ለበርካታ ዓመታት ሲታሰር ያሳየው መልካም ባህሪ፣ ሦስት ድግሪ ማግኘቱ እና የማኅበረሰብ ግልጋሎቱ መዝገቡን ለማየት ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት የሚል እምነት አለው።
"በጣም በጥልቅ የሚያበሳጨው የምናቅፍበት አፍታ እንኳ አላገኘንም" ትላለች እህቱ።
ቤተሰቦቹ የኢምግሬሽን ባለሥልጣኑ ሊያባርረው ያሰበው አገር ሕንድ ቪዳም ምንም ትስስር የለውም በሚልም ተጨንቀዋል።
ምንም እንኳ ሕንድ ቢወለድም በዘጠኝ ወሩ ወደ አሜሪካ መዛወሩን የተናገሩት ቤተሰቦቹ፤ በሕይወት ያሉ ዘመዶቹም ጋር የቅርብ ቅንኙነት እንደሌለው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እሁቱ፣ አራት የእህቱ ልጆች እና የአጎት ወይም የአክስቱ ልጆቹ አሜሪካ እና ከናዳ እንደሚኖሩን ገልፀዋል።
"ከዓለም ወዲያ ማዶ ሆኖ ከቅርቡ ሰዎች ጋር ያለውን ሕይወት አሁንም በድጋሜ ያጣል" የምትለው እህቱ፤ "ለሁለተኛ ጊዜ ሕይወትን የመነጠቅ ያህል ነው" ብላለች።
ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ቪዳም ከእስራቱ በፊት የዜግነት ማመልከቻው ተቃባይ ሆኖ ነበር። ሁለቱም ወላጆቹ የአሜሪካ ዜጎች ነበሩ።
ጠበቃው ኤቫ ቤንች ባወጡት መግለጫ "አሁን ከዩናይትድ ስቴትስ አነስተኛ ግንኙነት ወዳለው አገር ማባረር በፍትኅ መጓደል በደል የደረሰበትን ሰው በድጋሚ በደል መፈፀም እንደማለት ነው ብለን እናምናለን" ብለዋል።