ከአሜሪካ ተባርረው ጋና ውስጥ "በሕገወጥ መንገድ" ታስረናል ያሉ ስደተኞች ክስ መሠረቱ

ከአሜሪካ ተባርረው ጋና ውስጥ የታሰሩ 11 ሰዎች የአገሪቱን መንግሥት መክሰሳቸውን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ኦሊቨር ባርከር ቮርማዎር የተባረሩት ግለሰቦች የጋናን ሕግ ሳይጥሱ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸው ሕገ ወጥ ነው ብለዋል።

መንግሥት ግለሰቦቹን ፍርድ ቤት እንዲያቀርባቸው እና ያለ ፍላጎታቸው ለምን እንደተያዙ አንዲያስረዳ እንደሚፈልጉ ጠበቃው አክለው ተናግረዋል።

መንግሥት በክሱ ላይ እስካሁን ድረስ አስተያየቱን ያልሰጠ ሲሆን ነገር ግን ከዚህ በፊት ተጨማሪ 40 ከአሜሪካ የሚባረሩ ግለሰቦችን እንደሚቀበል አስታውቆ ነበር።

የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት የሕዝብ እንደራሴ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር የገባችውን ስምምነት እስኪያጸድቀው ድረስ በፍጥነት ስደተኞቹን መቀበሉ እንዲቆም ጠይቀው ይህ በጋና ሕግ መሠረት ተግባራዊ መሆን ያለበት ነው ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ማሃማ 14 የምዕራብ አፍሪካ ዜግነት ያላቸው እና ከዩናይትድ ስቴትስ የተባረሩ ስደተኞችን ከአሜሪካ ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት መቀበላቸውን አስታውቀው ነበር።

በማስከተልም ሁሉም ወደ የአገራቸው መላካቸውን የተናገሩ ቢሆንም የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩድዜቶ አብላክዋ ደግሞ አብዛኞቹ ብቻ መላካቸውን ተናግረዋል።

ጠበቃ ቮማዎር አሁንም 11 ስደተኞች በጋና በእስር ላይ እንደሚገኙ በፍርድ ቤት ማማልከቻቸው ላይ ገልፀው ሁለቱም የአገሪቱ ባለሥልጣናት ካሉት በተቃራኒ እየሆነ መሆኑን በአቤቱታቸው ላይ አካትተዋል።

ለፍርድ ቤት በቀረበው ማመልከቻ ላይ 11ዱም ወደ ጋና ታስረው እንዲመለሱ ከመደረጉ በፊት በአሜሪካ የስደተኞች ማቆያ ውስጥ ተቀምጠው እንደነበር ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ በሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ በወሰዱት ጠንካራ እርምጃ መሠረት የተለያዩ አገራት ስደተኞች ወደ አፍሪካ አገራት ተልከዋል።

ትራምፕ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕገ ወጥ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ቃል ገብተዋል።

የጋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ዕለት አገሪቱ ስደተኞቹን ለመቀበል ከውሳኔ ላይ የደረሰችው "በሰብዓዊነት መርሆዎች እና በፓን አፍሪካዊ ርህራሄ መሠረት ነው" ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

አክለውም "ይህ የትራምፕ አስተዳደርን የስደተኞች ፖሊሲን እንደመደገፍ ተደርጎ መተርጎም የለበትም" ብለዋል።

ከስደተኞቹ መካከል ሦስት ናይጄርያውያን እና ሁለት ጋምቢያውያን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከአገር እንዳንባረር ታግዶ ሳለ ተባረናል በሚል የአሜሪካን መንግሥት ከስሰዋል።