ቤላሩስ የአሜሪካ ማዕቀብ ከተነሳላት በኋላ 123 የፖለቲካ እስረኞችን ለቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቤላሩስ፣ አሜሪካ የጣለችባትን ማዕቀብ ለማንሳት መስማማቷን ተከትሎ ታዋቂዋን ተቃዋሚ አክቲቪስት ማሪያ ኮልስኒኮቫን ጨምሮ 123 እስረኞችን ለቀቀች።
በሚኒስክ እና በቤላሩስ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ በሆኑት ጆን ኮል መካከል ንግግር ከተደረገ በኋላ ከተለቀቁት እስረኞች መካከል የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው አሊስ ቢያሊያትስኪ ይገኙበታል።
በምላሹ አሜሪካ የአፈር ማዳበሪያ ለማዘጋጀት በሚውለው እና የሩሲያ የቅርብ አጋር የሆነችው ቤላሩስ በዋናነት ወደ ውጭ በምትልከው የፖታስየም ምርት ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለማንሳት ተስማምታለች።
በፖታሲየም ምርቷ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወዲያውኑ እንደሚነሳም የቤላሩስ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ልዩ መልዕክተኛውን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ መደበኛነት እየተመለሰ በመምጣቱ ሌሎች ማዕቀቦችም እንደሚነሱላት ልዩ መልዕክተኛው ተናግረዋል።
የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ የዩክሬን ጦርነትን በተመለከተ እንዲሁም ሚኒስክ ከፑቲን ጋር የሚደረገውን ንግግር በምን መልኩ ማገዝ እንደምትችል ከሉካሽንኮ ጋር መነጋገራቸውም ተገልጿል።
ከሚኒስክ ጋር ለመነጋገር የተደረገው ሙከራ የአሜሪካ ፖሊሲ ትልቅ ለውጥ አካል ሲሆን "ማግለልን እና ማዕቀብን" የተከተለው ዘዴ ግን ከአውሮፓ ጋር በብዙ የሚጋጭ ነው።
የቤላሩሱ መሪ አሌክሳንደር ሉካሽንኮም ፕሬዚዳንትነታቸው በአውሮፓ ኅብረት እውቅና አልተሰጠውም።
ከአውሮፓውያኑ 2020 ጀምሮ እስር ቤት ውስጥ ተገልላ የቆየችው ኮልስኒኮቫ፣ ከእስር ከተለቀቀች በኋላ "የምትወዳቸውን ሰዎች ማየት እና ማቀፍ በመቻሏ የማይታመን ደስታ" እንደተሰማት ተናግራለች።
"የሚያስገርም ውበት ያላትን የነጻነቴን የመጀመሪያዋን የፀሐይ ግባት ለመመልከት መታደሌ ትልቅ ደስታ ነው" ብላለች።
"እስካሁንም ያልተለቀቁትን እናስባቸዋለን ። ሁሉም ነጻ ሆነው እርስ በእርስ የምንተቃቀፍበትን ቀን እጠብቃለሁ" ስትልም አክላለች።
በኪዮቭ የጦር እስረኞችን አያያዝ የሚመለከተው ዋና መሥሪያ ቤት እንደገለጸው ከሆነ ኮልስኒኮቫን ጨምሮ 113 እስረኞች ለዩክሬን ተሰጥተዋል።
ዩክሬን በቴሌግራም ገጽ ላይ ባጋራችው መግለጫ እስረኞቹ የሚያስፈልገው የሕክምና እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ፖላንድ እና ሊቱኒያ መወሰዳቸውን አስታውቃለች።
ቤላሩሳዊቷ የተቃዋሚ መሪ ስቬትላና ቲክሃኖቭስካያ፣ "ወደ ዩክሬን እንዲላኩ የተወሰነው ውሳኔ ያልተጠበቀ እና በሉካሽንኮ የተወሰነ ውሳኔ እንደሆነ" በቪሊኒየስ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ውጭ ሆና ለቢቢሲ ተናግራለች።
የኖቤል የሰላም ተሻለሚውን ቢያሊያስቲክን ጨምሮ የተወሰኑ ቁጥር ያላቸው እስረኞችም ወደ ሉቲየኒያ መዲና ተወስደዋል። "በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል፤ መታሰራቸው ይቀጥላል፤ ስለዚህ ትግላችንም ይቀጥላል" ብለዋል ቢያሊያስቲክ።
የኮልስኒኮቫ እህት ታቲሲያና ኮልስኒኮቫ፣ ኮልስኒኮቫ በመጀመሪያ የአሜሪካን መንግሥት እና ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን ከቤላሩስ መንግሥት ጋር በመነጋገር ይህ ድርድር እንዲኖር በማድረጋቸው ምስጋና ማቅረቧን ተናግራለች።
ስምምነቱ ለሉካሽንኮ ትልቅ ስኬት ሲሆን አምባገነኑ መሪ ከዓለም የተገለሉበት ማዕቀብ መነሳቱን በመልካም ተቀብለዋል።
ከአውሮፓ ኅብረት በተጨማሪ አሜሪካም ከአምስት ዓመት በፊት የተካሄደውና የአደባባይ ተቃውሞ ያስከተለው ምርጫ ፍትሃዊ አይደለም በሚል ለሉካሽንኮ የፕሬዚደንትነት እውቅና አልሰጠችም።
ተቃውሞውን ተከትሎ ኮልስኒኮቫን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን ፖሊስም የሚፈፅመውን የኃይል ጫና ቀጥሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሰፊ ወረራ ከፈፀመች በኋላ ወታደሮች በቤላሩስ በኩል በመግባታቸው እና ከግዛቷ ሚሳኤሎች በመተኮሳቸው የምዕራባውያኑ ማዕቀብ በርትቶባት ነበር።
አሁን በተደረገው ስምምነት ከአምስት ዓመት በፊት ታስሮ የነበረው የቤላሩስ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቪክተር ባባርያኮ፣ የገለልተኛ የሚዲያ ገጽ ዋና አዘጋጅ ከሆነችው ከማሪና ዞሎቶቫ ጋር ቅዳሜ ዕለት ተፈትቷል።
ቲክሃኖቭስካያ አሜሪካ የፖታስየም ንግድ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በማንሳት በምላሹ እስረኞች እንዲለቀቁ ከቤላሩስ ጋር የገባችውን ስምምነት በተመለከተ አስተያየየት ስትሰጥ " ማዕቀቦቹ አምባገነኖች የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ነው" ብላለች።
ጨምራም "ሉካሽንኮ ሰብዓዊነት ስለሚሰማቸው አይደለም እስረኞችን የለቀቀው፤ ሰዎችን በሚቻለው ውድ ዋጋ መሸጥ ነው የፈለገው" ብላለች።
"እርግጥ ነው ዋጋው ይህ ነው። ሆኖም የአሜሪካ ማዕቀብ ተለዋዋጭ እንደሚሆን እንረዳለን። የሆነ ስምምነት ካልተሟላላቸው ነገ ደግሞ ሊያነሱት ይችላሉ" ስትል ተናግራለች።















