ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስህተት የሌላ ጥንዶችን ልጅ አርግዛ የወለደችው አሜሪካዊት ክስ መሰረተች
አሜሪካዊቷ እናት ሳታውቅ የራሷ ያልሆነን ወንድ ልጅ እንድታረግዝና እንድትወልድ ያደረገው የአይቪኤፍ (IVF) ክሊኒክ ላይ ክስ መሰረተች።
በጆርጂያ ግዛት የምትኖረው ክሪስቲና ሙራይ በግንቦት 2023 ወደ አንድ የወሊድ ክሊኒክ በመሄድ የIVF ሕክምና ከወሰደች በኋላ ጸንሳለች።
ነገር ግን የተሸከመችው ፅንስ የሌላ ባልና ሚስት መሆኑ የታወቀው ሙሬይ ከእርሷ እና ከመረጠችው የወንድ ዘር ለጋሽ የተለየ ዘር የሆነ ወንድ ልጅ በሰላም ከተገላገለች በኋላ ነው።
ስህተቱ ቢፈጠርም ሙሬይ ልጁን ማሳደግ ፈልጋ ስለነበር ወላጆቹ ሕጋዊ የማሳደግ መብት እስኪያገኙ ድረስ ሕፃኑን ለብዙ ወራት አሳደገች።
ሙሬይ በጠበቃዋ በኩል በሰጠችው መግለጫ "ማርገዝ፣ ከጽንሱ ጋር በፍቅር መውደቅ፣መውለድ ከዚያም ከልጁ ጋር ልዩ የሆነ መስተጋብር መፍጠር፣ እንዲሁም ከእቅፍ መነጠቅ ሕመም አለው። ከዚህ ሙሉ በሙሉ ላገግም አልችልም" ብላለች።
ሙሬይ፣ ነጭ ብትሆንም በታህሳስ 2023 ጥቁር ሕፃን ነበር የወለደችው። የልጁን ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላጋራች ሲሆን ጓደኞቿ እና ቤተሰቦቿ እንዲያዩትም አልፈቀደችም።
በመጨረሻ በቤት ውስጥ የዲኤንኤ መመርመርያ ገዝታ እና በጥር 2024 መጨረሻ ያገኘችው የምርመራ ውጤት ከልጇ ጋር ምንም ዓይነት ስነ ህይወታዊ ትስስር እንደሌላት እንደሚያሳይ በክሊኒኩ ላይ ያቀረበችው ክስ ዝርዝር ያስረዳል።
በሚቀጥለው ወር ስለ ተፈጠረው ስህተት ለክሊኒኩ ያሳወቀች ሲሆን፣ ሕፃኑ የሦስት ወር ልጅ እያለ ለወላጆቹ በመነገሩ እነርሱም ወድያውኑ የአሳዳጊነት መብታችን ይረጋገጥ ሲሉ ክስ መስርተዋል።
ሙሬይ በፍርድ ቤት ተከራክራ የማሸነፍ እድል እንደሌላት በጠበቆቿ ከተነገራት በኋላ በገዛ ፍቃዷ ከችሎት ክርክር ራሷን አውጥታለች።
ሕፃኑ አሁን ከወላጆቹ ጋር በተለየ ስም በሌላ ግዛት መኖር ጀምሯል።
ሙሬይ ክሊኒኩ ላይ ባቀረበችው ቅሬታ መሰረት እስከ ዛሬ ድረስ ክሊኒኩ፣ እንቁላሏን በስህተት ለሌላ ጥንዶች ይስጥ አልያም ከዚያ በኋላ ምን እንደተፈጠረ የምታውቀው ነገር የላትም።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር እንደዘገበው የወሊድ ክሊኒኩ ስህተቱን አምኖ ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ ጠይቋል ብሏል።
መግለጫው "ይህ ምንም ተጨማሪ ደንበኛ የሌለበት ገለልተኛ ክስተት ነበር" ይላል።
"ይህ ስህተት በታወቀበት በዚያው ዕለት ጥልቅ ግምገማ አካሂደን፣ታማሚዎችን የበለጠ ለመጠበቅ እና እንደዚህ አይነት ክስተት እንደገና እንዳይከሰት ለማረጋገጥ ተጨማሪ መከላከያዎችን አስቀምጠናል።"
በአሜሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በወሊድ ክሊኒኮች ላይ የሴቴ ዘር እንቁላል እና የወንድ ዘር እየተደባለቀ ብዙ ክሶች ተመስርተዋል።
IVF የሴቷ አንእቁላል ከወንዱ ዘር ጋር በላቦራቶር ውስጥ ተገናኝቶ ጽንስ እንዲፈጠር ከተደረገ በኋላ በሴቷ ማሕጸን ውስጥ ተቀምጦ ቀሪውን እድገቱን የሚያከናውንበት የሕክምና ዓይነት ነው።