ካንሰር ያለባቸውን ሕፃናት በመጠቀም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰቡን የቢቢሲ ምርመራ አጋለጠ

ፊሊፒንሳዊው ኻሊል ለእርዳታ ማሰባሰቢያ ከተቀረፀው ቪድዮ የተወሰደ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Chance Letikva

የምስሉ መግለጫ, ኻሊል ለእርዳታ ማሰባሰቢያ ቪድዮ የተቀረፀው ፀጉሩን እንዲላጭ ተደርጎ ነው

ማስጠንቀቂያ፡ የሚረብሽ ይዘት

አንድ ሕፃን ልጅ ካሜራ ፊት ቆሟል። ፊቱ ገርጣ ብሏል። ፀጉርም የለውም።

"እኔ ሰባት ዓመቴ ነው። ካንሰር አለብኝ" ይላል። "እባካችሁ ሕይወቴን ታደጓት። እርዳታ አድርጉልኝ።"

ከላይ በምስሉ የሚታየው ኻሊል መቀረፅ አልፈገም ነበር ትላለች እናቱ አልይን።

ፀጉሩን እንድትላጨው፣ ሀሰተኛ የኦክስጅን መስጫ ቱቦ አፍንጫው ላይ እንድታደርግለት እና ልደቱ እንደሆነ እንድታስመስል ፊልሙን የሚሰሩት ሰዎች ነግረዋታል። ካሜራ ላይ የሚለው ነገር በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተፅፎ ተሰጥቶታል።

እያለቀሰ እንደሆነ ለማስመሰል ተልጦ የተከተፈ ሽንኩርት እና ሜንቶል ተሰጠው።

የተደረገው ሁሉ የተቀነባበረ ቢሆንም ኻሊል ግን የካንሰር በሽተኛ ነበር። በኻሊል ስም የተዋጣው ገንዘብ 27 ሺህ ዶላር ገደማ እንደሆነ ቢቢሲ ደርሶበታል።

ነገር ግን ለአልይን የተነገራት መዋጮው እንዳልተሳካ ነው። ምንም የደረሳት ገንዘብ የለም። ለፊልም ቀረፃው ብቻ 700 ዶላር ተሰጣት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአንድ ዓመት በኋላ ሞተ።

የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ እንደሚያሳየው በመላው ዓለም በሽተኛ ልጅ ያላቸው ቤሰተቦችን ተጠቅመው ገንዘብ የሚያጭበረብሩ ብዙዎች ናቸው።

በርካቶች ባለማወቅ እርዳታ እየሰበሰብን ነው ለሚሉ ሰዎች ገንዘባቸውን ሰጥተዋል።

ከተሰበሰበው እርዳታ ጥቂት ገንዘብ ያገኙ አሊያም ቤሳቤስቲ ያላገኙ እንዲሁም የእርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻ እየተደረገ እንዳለም የማያውቁ 15 ቤተሰቦችን አግኝተናል።

ከእነዚህ መካከል 9 ቤተሰቦች በተመሳሳይ ኔትዎርክ የተጨብረበሩ ሲሆን በስማቸው 4 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ቢሰበሰብም የደረሳቸው በጣም ጥቂት ነው።

የዚህን ኔትዎርክ ምስጢር ያሾለከ የድርጅቱ ሠራተኛ እንደሚለው "መልከ መልካም" እና "ከሦስት እስከ ዘጠኝ ዓመት ያሉ. . . ፀጉር የሌላቸው ሕፃናት" እንደሚመረጡ ይናገራል።

በዚህ ማጭበርበር ሒደት ቁልፍ የተባለ ካናዳ የሚኖር ኤሬዝ ሀዳሪ የተባለ እስራኤላዊ እንዳለ ተረድተናል።

ምርመራችን የጀመረው በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2023 ነው።

አንድ የሚረብሽ የዩቲዩብ ማስታወቂያ ቀልባችንን ገዛው።

"መሞት አልፈልግም" ትላለች አንዲት አሌክሳንድራ የምትባል ጋና ያለች ሕፃን። "ሕክምናየ ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል።"

ለሷ የተዋጣው ገንዘብ ወደ 700 ሺህ ዶላር ገደማ ይሆናል።

ዩቲዩብ ላይ የተለያዩ ዓለማት የሚገኙ የበሽተኛ ሕፃናት ቪድዮዎች ተለጥፈዋል። ብዙዎች የሚያመሳስል ነገር አላቸው። በጥንቃቄ የተቀረፁ ናቸው። በርካታ ገንዘብ ተዋጥቶላቸዋል። የሚጠቀሙት ቋንቋ ስሜት ቀስቃሽ እና በፍጥነት እርዳታ እንዲሰባሰብ የሚያደርግ ነው።

ምርመራችንን አጠናክረን ቀጠልን።

ዘመቻዎቹ የሚከናወኑት ቻንስ ሌቲክቫ በተባለ ድርጅት አማካይነት ነው። ድርጅቱ በእስራኤል እና አሜሪካ የተመዘገበ ነው።

ቪድዮው ላይ የሚታዩትን ሕፃናት መለየት ከባድ ነበር። ጂኦሎኬሽን፣ ማኅበራዊ ሚድያ እና የፊት ገፅ መለያ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወላጆችን ለማግኘት ሞከርን።

እነዚህ ወላጆች ከኮሎምቢያ እስከ ፊሊፒንስ የሚገኙ ናቸው።

አና እና አባቷ ሰርጂዮ ፈረስ ሲጋልቡ
የምስሉ መግለጫ, አና እና አባቷ ሰርጂዮ

የእርዳታ ማሰባሰቢያው ድረ-ገፅ በእርግጠኝነት ምን ያክል ገንዘብ እንደተዋጣ ያሳያል ወይ የሚለውን ለማወቅ በሁለት ድረ-ገፆች ላይ አነስተኛ ገንዘብ ስናዋጣ ባዋጣነው መጠን ሲጨምር አየነው።

በፊሊፒንስ አልይን ታባሳ ልጇ ኻሊል ሰባተኛ ዓመቱን ካከበረ በኋላ ክፉኛ እንደታመመ ነገረችን።

"ካንሰር እንደሆነ ባወቅን ጊዜ ሁሉም ነገር ጨለመብን" ትላለች።

እናት እንደምትለው በምትኖርበት አካባቢ ያለው ሕክምና በቂ ባለመሆኑ የምታውቃቸውን ሰዎች ሁሉ ለእርዳታ ተማፅናለች። በሰው በሰው ያገኘችው አንድ ግለሰብ የኻሊልን ቪድዮ እንድትልክለት ጠየቃት። ጉዳዩ ምልመላ መሆኑ የገባት ከዘገየ በኋላ ነው።

በ2022 አንድ ከካናዳ የመጣ ግለሰብ ራሱን "ኤሬዝ" ብሎ አስተዋወቃት። ለቀረፃ የሚሆን ገንዘብ ከሰጣት በኋላ ቪድዮው ገንዘብ የሚያመጣ ከሆነ በየወሩ 1500 ዶላር ሊሰጣት ቃል ገባላት።

ኤሬዝ በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል የኻሊልን ቪድዮ ቀረፀ። ቀረፃው 12 ሰዓታት አካባቢ እንደወሰደ አልይን ትናገራለች።

ቪክቶሪያ እና እናቷ ኦሌና
የምስሉ መግለጫ, ቪክቶሪያ እና እናቷ ኦሌና

ወራት ቢቆጠሩም ቤተሰቡ ቪድዮው የት ደረጃ እንደደረሰ ማወቅ አልቻሉም። ኤሬዝ ለአልይን ቪድዮውን "ስኬታማ አይደለም" ሲል መልዕክት ላከላት።

ነገር ግን የእርዳታ ዘመቻው እስከ አውሮፓውያኑ ኅዳር 2024 ድረስ 27 ሺህ ዶላር ገደማ አሰባስቧል።

"የተዋጣለትን ገንዘብ ባውቅ ኖሮ ምናልባትም ኻሊል አሁንም በሕይወት ይኖር ነበር። እንዴት ይህን ነገር እኛ ላይ ሊያደርጉ እንደቻሉ አልገባኝም።"

ቻንስ ሌቲክቫ የተሰኘው ድርጅት ውስጥ ኤሬዝ የሚባል ሰው ስም አልተጠቀሰም። ነገር ግን ሁለት ሌሎች የእርዳታ ማሰበሳቢያ ቪድየዎች ዎልስ ኦፍ ሆፕ በተሰኘ ድርጅት ነው የተዋወቁት። ድርጅቱ በካናዳ እና እስራኤል የተመዘገበ ነው። መዛግብት እንደሚያሳዩት የድርጅቱ የካናዳ ዳይሬክተር ኤሬዝ ሀዳሪ የተባለ ግለሰብ ነው።

ኢንተርኔት ላይ የተለጠፉ የሰውየው ፎቶዎች በፊሊፒንስ፣ ኒው ዮርክ እና ማያሚ የአይሁዳዊያንን በዓል ሲያከብር ያሳያሉ። ፎቶውን ለአልይን ስናሳያት የተዋወቀችው ግለሰብ እሱ መሆኑን ነገረችን።

በፊሊፒንስ ስለተካሄደው የእርዳታ ዘመቻ ሀዳሪን ብንጠይቀውም ምላሽ አሰልሰጠም።

በኮሎምቢያና እና በዩኬሬንም በተመሳሳይ የእርዳታ ጥሪ የሚያቀርቡ ቪድዮዎች ተቀርፀዋል።

በኮሎምቢያ የስምንት ዓመቷ አና የካንሰር በሽተኛ ናት። ኢዛቤል የተባለች ግለሰብ አባቷ ሰርጂዮ ካሬን ቀርባ አንድ ግለሰብ ሊረዳው እንደሚፈልግ ነገረችው። ሰውየው መጥቶ ሰርጂዮና ልጁን ጎብኝቶ ተመልሷል።

የኤሬዝን ፎቶ ለሰርጂዮ ስናሳየው ኤሬዝ መሆኑን አረጋግጦልናል።

የአና ቪድዮ እስከ ሚያዚያ 2024 250 ሺህ ዶላር ማሰባሰብ ችሏል። ነገር ግን ለአና ቃል የተገባላት ገንዘብ አልደረሳትም። እርግጥ አና አሁንም ከበሽታዋ ሙሉ በሙሉ አገግማለች።

ኢዛቤል ለጥያቄችን ምላሽ ሰጠች። እስራኤል የሚገኝ ጓደኛዋ ኤሬዝን እንዳስተዋወቃት ብትገልፅም ስለጉዳዩ እንደማታውቅ ትናገራለች።

"ለቤተሰቦቹ ይቅርታ መጠየቅ እሻለሁ። ምን እየተከናወነ እንዳለ ባውቅ ኖሮ በፍፁም ይህን አላደርገውም ነበር" ትላለች።

በዩክሬን ደግሞ ለአምስት ዓመቷ ቪክቶሪያ የተዋጣው ገንዘብ 280 ሺህ ዶላር አካባቢ ነው።

ኤሬዝ ሀዳሪ ይህን ፎቶውን ለኻሊል እናት አልይን የላከው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Erez Hadari

የምስሉ መግለጫ, ኤሬዝ ሀዳሪ ይህን ፎቶውን ለኻሊል እናት ልኳል

ለኻሊል እና ሄክተር ለተሰኘ ሜክሲኮ ለሚገኙ ሕፃናት ገንዘብ የሚሰባሰብበት ድረ-ገፅ አሁንም እርዳታ እየተቀበለ እንደሆነ ማየት ችለናል። ሁለቱም ሕፃናት ሞተዋል።

የቻንስ ሌቲክቫ የአሜሪካ ቅርንጫፍ ሴይንት ራፋኤል ከተባለ አዲስ ድርጅት ጋር ግንኙነት ያለው ይመስላል።

ቢቢሲ ሁሉንም በመሰል የገንዘብ ማሰባሰብ ማጭበርበር ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች ጥያቄ ቢልክም አንዳቸውም ምላሽ አልሰጡም።

እርዳታ አሰባሳቢ ድርጅቶችን የሚቆጣጠረው የእስራኤል መንግሥት መሥሪያ ቤት አንዳንድ ድርጅቶች "ለሕገ-ወጥ ሥራቸው" ድርጅት እንደሚመሰርቱ ማስረጃው እንዳለው ይናገራል።

የዩናይትድ ኪንግደም ቻሪቲ ኮሚሽን ደግሞ እርዳታ የሚለግሱ ሰዎች ገንዘብ ሲሰጡ ድርጅቶችን በጥንቃቄ እንዲመለከቱና ጥርጣሬ ካላቸው ጥቆማ እንዲያደርጉ አሳስቧል።