የቀድሞ የብራዚል ተጫዋች ሮቢንሆ በመድፈር ወንጀል የ 9 ዓመት እስር ተፈረደበት

ዕውቁ የብራዚል ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች ሮቢንሆ በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የዓመታት አስር ተፈረደበት።

ከብራዚል ኮከብ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው ሮቢንሆ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በጣልያን ፍርድ ቤት የዘጠኝ ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ሮቢኒሆ እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 በጣልያን ሚላን ከተማ በሚገኝ የምሽት የመዝናኛ ክበብ ውስጥ የአልቤኒያ ዜግነት ያላት ሴት በቡድን ስትደፈር ተሳታፊ ነበር ተብሏል።

አሁን የ40 ዓመት ጎልማሳ የሆነው ሮቢንሆ በብራዚል ሳንቶስ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ የቁም እስረኛ ሆኖ ቆይቷል።

ጣልያን የብራዚል መንግሥት የቀድሞው ተጫዋች ለፈጸመው ወንጀል አሳልፎ እንዲሰጠው ቢጠይቅም፣ ብራዚል ለዚህ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ሮቢንሆ ቅጣቱን እዚያው እንዲቀበል ጠይቋል።

በዚህ ሳምንት አጋማሽ የብራዚል ፍርድ ቤት የጣልያን ችሎት ተጫዋቹ ላይ የጣለውን ቅጣት አጽንቷል።

በተጨማሪም የተላለፈበትን እስር በቁም እስር ሳይሆን በመደበኛ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ እንዲያሳልፍም ወስኗል።

ባለፈው ማክሰኞ የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሮቢኒሆ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ እንዲያግድ ጥያቄ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም ውድቅ አድርጎታል።

ሮቢንሆ የተጣለበትን ቅጣት በብራዚል እንዲያሳልፍ መወሰኑ በበርካታ የብራዚል መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኗል። መገናኛ ብዙኃኑ ሮቢኒሆ በገንዘቡ እና ቤተሰቦቹ አማካኝነት ከተጣለበት እስር ሊያመልጥ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሮባቸዋል።

የቀድሞ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሮቢንሆ ለአገሩ 100 ጊዜ ተሰልፎ መጫወት ችሏል። ወንጀሉ በተፈጸመበት ጊዜ ለጣልያኑ ኤስ ሚላን እግር ኳስ ክለብ ይጫወት ነበር።

ሮቢንሆ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ በአሮፓውያኑ 2020 ለጣልያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቀ ቢሆንም፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ባሳለፈው ውሳኔ ፍርዱን አጽንቶታል።

ከዚህ በኋላ ነው የጣልያን ዐቅቢያነ ሕጎች ተጫዋቹ ላይ ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ ያወጡበት።

ለማንቺስተር ሲቲ ለሁለት ዓመታት የተጫወተው ሮቢንሆ ባለፈው እሁድ ለአንድ የብራዚል ሚዲያ በሰጠው አስተያየት ወንጀል አልፈጸምኩም ያለ ሲሆን “በፍቃደኝነት የተደረገ ግንኙነት ነው” ብሏል።