ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ እንደራሴዎች አፈጉባኤ ለመምረጥ መስማማት ስላልቻሉ ተፋጠዋል
የአሜሪካ አዲሱ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት እንደራሴዎች አፈ ጉባኤ ለመምረጥ ተስኗቸዋል።
በዚህ የተነሳ የታችኛው ምክር ቤት አዲስ የሥራ ዘመን ሊጀመር አልቻለም።
ምክር ቤቱን በአፈ ጉባኤነት ማን ይምራው በሚለው ላይ ሊስማሙ ባለመቻላቸው 434 አባላት ቃለ መሐላ ፈጽመው ወደ ሥራ መግባት አልቻሉም።
ምክር ቤቱ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲገጥመው በመቶ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የ82 ዓመቷ ናንሲ ፒሎሲን የሚተካና ምክር ቤቱን የሚያስማማ አፈ ጉባኤ ለመምረጥ አስቸጋሪ የሆነው የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች ለሁለት በመሰንጠቃቸው ነው።
ለአፈ ጉባኤነት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ሪፐብሊካኑ የካሊፎርኒያ ተወካይ ኬቨን ማካርቲ 20 በሚሆኑ አፈንጋጭ የፓርቲያቸው ሰዎች ድምጽ በመነፈጋቸው ሥልጣኑን ሊያገኙት ጫፍ ደርሰው እያጡት ነው።
በአሜሪካ ሕግ አንድ አፈ ጉባኤ ከጠቅላላ ድምጽ ከሚሰጡ እንደራሴዎች በትንሹ 218 ድጋፍ ማግኘት አለበት።
ያን ድምጽ ካላገኘ ለአፈ ጉባኤነት አይበቃም።
አፈ ጉባኤ ካልተመረጠ ደግሞ የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱ ሥራ መጀመር አይችልም።
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ አፈ ጉባኤ መርጠው ቃለ መሐላ ለመፈጸም ካፒቶል ሒል አምረውና ደምቀው፣ ቤተሰባቸውን አስከትለው የተገኙ እንደራሴዎች ቀኑን ሙሉ ድምጽ እየሰጡ ቢውሉም ያሰቡት ሳይሳካ በታላቅ ሐዘን ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።
በዚያ ዕለት ብቻ የምክር ቤቱ አባላት ምናልባት ከተሳካ በሚል ለሦስት ዙር ድምጽ ሰጥተዋል።
ይህ ረዥም ሰዓታትን የወሰዱ ሂደት ፍሬ አላፈራም። ሦስቱንም ጊዜ አብላጫ ድምጽ ማግኘት የቻለ ዕጩ አልነበረም።
ትናንት ረቡዕ ለሁለተኛ ቀን ሌላ ሦስት ዙር ድምጽ የመስጠት የተራዘመ ሂደት ቢደረግም ማካርቲ የሚያስፈልጋቸውን ድምጽ ማግኘት ተስኗቸዋል።
‘ምን ይሻላል ታዲያ?’ በሚል ምክር ቤቱ ለጊዜው እንዲበተን እና ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት ለ3ኛ ቀን፣ ለ7ኛ ዙር ድምጽ የመስጠት ሙከራ እንዲያደርግ ከስምምነት ተደርሷል።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ በድምሩ 435 አባላት አሉት። ከእነዚህ መካከል 222 የሚሆኑት ሪፐብሊካኖች ሲሆኑ 213 የሚሆኑት ደግሞ ዲሞክራቶች ናቸው።
ይሁንና ጥቂት አክራሪ የዶናልድ ትራምፕ አፍቃሪዎች ለኬቨን ማካርቲ ድምጽ አንሰጥም በማለታቸው ምክር ቤቱን የተከታታይ ድራማ መድረክ አድርገውታል።
ዲሞክራቶች በበኩላቸው ለአፈ ጉባኤነት በመታጨት የመጀመሪያ ጥቁር ያሉትን ሐኪም ጄፍሪስን በዕጩነት አቅርበዋል።
ሐኪም ጄፍሪስ 6 ጊዜ በተደረገው ድምጽ አሰጣት ከሪፐብሊካኑ ኬቨን ማካርቲ የተሻለ ድምጽ እያገኙ ሲሆን፣ የዲሞክራቶች ቁጥር በምክር ቤቱ አነስተኛ ስለሆነ ግን ለአፈ ጉባኤነት የሚያበቃ ሙሉ ድምጽ ሊያገኙ አልቻሉም።
አመጸኛ የተባሉት እና ከ20 የማይበልጡትን የሪፐብሊካን አክራሪ አባላት ለኬቨን ማካርቲ ድምጽ እንዲሰጡ ሊያግባቡ የሚችሉት ብቸኛ ሰው ዶናልድ ትራምፕ በመሆናቸው እርሳቸው አንድ ነገር እንዲያደርጉ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ አክራሪዎቹን ሪፐብሊካኖች እንዲገስጹም ጫና ተደርጎባቸዋል።
ትራምፕ ለእነዚህ አፈንጋጮች “ድምጻችሁን ለማካርቲ ስጡ” ብለው መክረዋቸውም ነበር።
ይህ የሆነው ትናንት ረቡዕ ከሰዓት ነው።
የዶናልድ ትራምፕ ምክር መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ሲጠበቅ በተቃራኒው አፈንጋጮቹ ብሶባቸዋል።
አክራሪዎቹ እንደራሴዎች አርአያችን የሚሏቸውን ዶናልድ ትራምፕንም ለመስማት በፍጹም አልፈቀዱም።
ሁሉም ድምጽ እየሰጡ ያሉት ከማካርቲ ሌላ ስማቸው እምብዛምም ለማይታወቁ የሪፐብሊካን ዕጩዎች ነው።
ይህን እያደረጉ ያሉት ኬቨር ማካርቲ አፈ ጉባኤ ሆነው እንዳይመረጡ ለማድረግ ነው።
ዛሬ ሐሙስ በዋሺንግተን ሰዓት አቆጣጠር ቀትር ላይ ለ7ኛ ዙር አፈ ጉባኤ ለመምረጥ ድምጽ የመስጠት የተራዘመ ሂደት ይቀጥላል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ላይ መስማማት ካልቻለ እንደራሴዎቹ ቃለ መሐላ ፈጽመው ወደ ሥራ ሊገቡ ሕግ አይፈቅድም።
ስለዚህ የወሰደውን ጊዜ ይውሰድ ድምጽ አሰጣጡ ይቀጥላል።
አሁን ምናልባት ኬቨን ማካርቲ የሚፈለገውን 218 ድምጽ ማግኘት ከተሳናቸው ከውድድሩ ራሳቸውን እንዲያገሉ ፓርቲው ሊመክራቸው አልያም ጫና ሊፈጥርባቸው ይችላል።
ሌላው ብቸኛ አማራጭ የሚሆነው ግን የዲሞክራት እንደራሴዎች ድምጻቸውን ለኬቨን ማካርቲ ለመስጠት ከፈቀዱ ነው።
ይህን ለማድረግ ግን ፈጽሞ ፍቃደኛ አይደሉም። ማካርቲም ቢሆን ከዲሞክራቶች ድምጽ እንዲሰጣቸው ብዙም አይሹም።
ምክንያቱም ያ ከሆነ በገዛ ፓርቲያቸው የፖለቲካ ኪሳራን ያስከትልባቸዋልና ነው።
የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይህን ፖለቲካዊ ድራማ በየዕለቱ ለተመልካች በቀጥታ በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ።