የአሜሪካ ሠራዊት በአገራት ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያደርግ እንደነበር ተነገረ

የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት (ፔንታገን)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት (ፔንታገን)

ፌስቡክን ጨምሮ የበርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መድረኮች ባለቤት የሆነው ሜታ ለሥራው ስጋት ስለሆኑ ጉዳዮች ባወጣው ሪፖርት “ከአሜሪካ ሠራዊት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች” በበይነ መረብ ላይ ከሚካሄዱ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አመለከተ።

ይህ የመጀመሪያ ነው ያለው ግዙፍ አሜሪካንን የሚደግፍ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በሆነው በሜታ እንዲወገድ መደረጉን ባለፈው ነሐሴ ወር ገለልተኛ የመርማሪዎች አሳውቀው ነበር።

የፕሮፓጋንዳ ዘመቻው አሜሪካንን እና አጋሮቿን የሚደግፍ ሲሆን፣ ሩሲያን፣ ቻይናን እና ኢራንን የመሳሰሉ አገራትን ደግሞ የሚቃወም ነው።

ነገር ግን ባለሙያዎች እንዳሉት ዘመቻው እምብዛም ውጤታማ አልነበረም።

ሜታ በወሰደው እርምጃም ከፌስቡክ 39 አካውንቶች፣ 16 ገጾች እና ሁለት ቡድኖች እንዲሁም ኢንስታግራም ላይ ደግሞ 26 አካውንቶች “የተቀናጀ ሃቀኛ ያልሆነ ባህርይ” የሚለውን ፖሊሲ በመተላለፋቸው እንዲወገዱ ተደርገዋል።

“ይህ ዘመቻም መነሻው ከአሜሪካ ነው ሲል” ሜታ አስታውቋል።

ዘመቻው በስፋት ለፕሮፓጋንዳ የሚውሉትን የሌሉ ሰዎችን፣ የፈጠራ ምስሎችን፣ የተለወጠ የሴት ተዋናይት ምስልን በመጠቀም እንዲሁም በበርካታ የትስስር መድረኮች ላይ የሚካሄድ ነበረ።

ትኩረት የተደረገባቸው አገራትም አፍጋኒስታንን፣ አልጄሪያን፣ ኢራንን፣ ኢራቅን፣ ካዛክስታን፣ ሩሲያን፣ ሶማሊያን፣ ሶሪያን፣ ታጂክስታንን፣ ኡዝቤክስታንን እና የመንን የሚጨምር እንደሆነም ተነግሯል።

የረጅም ጊዜ የአሜሪካ ባላንጣ በሆነችው የባሕረ ሰላጤው አገር ኢራንን ኢላማ ያደረጉ አካውንቶች የአገሪቱን ባለሥልጣናት እና ፖሊሲያቸውን የሚተቺ ሲሆን፣ የሴቶችን መብት የመሳሰሉ ጉዳዮችንም እንደሚያነሱ ምርመራውን ያደረጉት ባለሙያዎች ጠቅሰዋል።

አሜሪካንን የሚደግፉ አንዳንዶቹ እራሳቸውን እንደ ነጻ ሚዲያ የሚያቀርቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ለቢቢሲ ሩሲያ ቋንቋ አገልግሎትን ለመሳሳሉ የታወቁ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መረጃዎችን ለማቀበል ይሞክራሉ።

ሜታ እንዳለው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻው ትዊተርን፣ ዩቲዩብን፣ ቴሌግራምንና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮችንም ጨምሮ ይጠቀማል።

“ከዘመቻው ጀርባ ያሉት ሰዎች ማንነታቸውን እና ያላቸውን ቅንጅት ለመደበቅ ቢሞክሩም፣ ያደረግነው ምርመራ ግለሰቦቹ ከአሜሪካ ሠራዊት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ደርሶበታል” ብሏል የምርመራው ሪፖርት።

ሜታ አሁን ይፋ ያደረገው ሪፖርት ቀደም ሲል በዋሽንግተን ፖስት በጉዳዩ ላይ የወጣውን ዘገባ ያረጋገጠ ሆኗል። የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት በድብቅ በሚካሄደው የመረጃ ጦርነት ዙሪያ ምርመራ እንዲያካሂድ ማድረጉን ምንጮች ለጋዜጣው ተናግረዋል።