አሜሪካ በዚምባብዌ አመራሮች ላይ አዲስ ማዕቀብ ጣለች

አሜሪካ በዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ላይ በሙስና እና በሰብዓዊ መብት ረገጣ ምክንያት አዲስ ማዕቀብ ጣለች።

ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችን የሚነካው ማዕቀብ በአሜሪካ ያሉ ንብረቶቻቸውን ማገድ እንዲሁም ጉዞ ማድረግን የሚከለክል ነው።

አዲሱ ማዕቀብ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በአገሪቱ ተጥሎ የነበረውን ሰፊ ማዕቀብም ተክቷል።

“በአገሪቱ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ጥሰቶችን እያየን ነው” ሲልም ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

“የሲቪል ማህበረሰቡ ኢላማ መደረጋቸውን እንዲሁም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የተጣለው ከባድ እገዳ መሰረታዊ ነጻነቶችን ጨፍልቀዋል። የመንግሥት መሪዎችን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት የህዝብን ሃብት ለግል ጥቅማቸው በዝብዘዋል” ሲልም አክሏል።

“እነዚህ ህገወጥ ተግባራት በዚምባብዌ፣ ደቡባዊ አፍሪካ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉ ማህበረሰቦችን ለድህነት የሚዳርግ፣ አለም አቀፍ የወንጀል መረብን የሚያሰፋ እንዲሁም ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርም ላይ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው” መግለጫው አትቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው በዚምባብዌ እየተከሰቱ ያሉ “በርካታ የጠለፋዎች፣ የአካል ጥቃቶች እና የዘፈቀደ ግድያዎች ነዋሪዎችን በፍርሃት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል” ብለዋል።

ዋይት ሐውስም “ለዚህ ብዝበዛ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች እና አካላት የሚጠየቁበትን ሁኔታ ለመዘርጋት ጥረቱን ከፍ እያደረገ ነው” ብሏል።

ማዕቀቡ ከፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ በተጨማሪ ሌሎች 10 ሰዎች እና ሶስት የንግድ ድርጅቶችን ይመለከታል።

በዝርዝሩ ውስጥ ከተካቱት መካከል ቀዳማዊት እመቤት ኦክሲሊያ ምናንጋግዋ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦፓህ ሙቺንጉሪ ይገኙበታል።

የዚምባብዌ ብሄራዊ ፖሊስ እና የማዕከላዊ መረጃ ድርጅአት (ሲአይኦ) አባላትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣት እንዲሁም የመንግሥት ሙስናን ሲያመቻቹ የነበሩ ነጋዴዎች ማዕቀቡ ኢላማ አድርጓቸዋል።

በተጨማሪም የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ኩዳክዋሼ ታግዊሬይ፣ ባለቤታቸው እና ሁለት የንግድ ድርጅቶቻቸውም በማዕቀብ ዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱበት ይገኙበታል።

ከዚህ ቀደም ቀደም በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸው የነበሩ እና በአዲስ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ ባለስልጣናት የነበረባቸው እገዳ ተነስቶላቸዋል።

የዚምባብዌ መንግሥት ቃል አቀባይ ኒክ ምናንጋግዋ የቀድሞው ማዕቀብ መነሳት የፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከፍተኛ ስኬት ነው ሲሉ ገልጸው አዲሱን ማዕቀብ “ህገወጥ” ሲሉ ገልጸውታል።

የገዥው ፓርቲ የዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ቃለ አቀባይ ፋራይ ሙሮይዋ ማራፒራ በበኩላቸው የፕሬዚዳንቱ “የሁሉም ወዳጅ እና ጠላትነትን የማክሰም ፖሊስ እንዲሁም አገሪቱ በሯን ለሁሉም ክፍት እንዲሆን መደረጉ አሳዛኝም፣ አስደሳችም ውጤት አስገኝቷል” ብለዋል።

ሆኖም “ፕሬዚዳንቱ፣ ቀዳማዊት እመቤት እና ከፍተኛ ባለስልጣናቱ ማዕቀብ ከተጣለባቸው የአገሪቱ ማዕቀብ ይቀጥላል፤ ይህ ህገወጥ ሸክም ይሆንባታል” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

አሜሪካ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እና በርካታ ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት የአገሪቱን ዲሞክራሲ በመናድ የኢኮኖሚ እና የጉዞ ማዕቀብ ጥላ ነበር።

የዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ህብረት አባላትን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በዚምባብዌ ላይ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።