ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመድ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ የዓለም ህዝብን ህሊና የጎዳ ነው አለ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ የዓለምን ህዝብ ህሊና የተፈታተነና የጎዳ ነው ሲሉ ተናገሩ።
ነገ የካቲት 17 አንድ ዓመት የሚደፍነውን ጦርነት አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ላይ ነው ዋና ጸሃፊው ይህንን የተናገሩት።
ስብሰባው ሩሲያ በአስቸኳይ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ራሷ እንድትወጣ አስገዳጅ ሁኔታን ለመፍጠር ዩክሬንና አጋሮቿ ባቀረቡት ሃሳብ ላይ ተወያይቷል።
ዩክሬን የቀረበውን ሃሳብ ሃገራቱ በመደገፍ አጋርነትን እንደሚያሳዩም ተስፋ ሰንቃለች።
ሩሲያ በበኩሏ የምዕራቡ ዓለም ማንኛውንም መንገድ ተጠቅመው ሩሲያን ማንበርከክ ይፈልጋሉ ስትል ከሳለች።
በተባበሩት መንግስታት የሩሲያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዛ እንዳሉት አሜሪካ እና አጋሮቿ መላውን አለም በጦርነቱ ለማሳተፍ ተዘጋጅተዋል ሲሉም ወቅሰዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ትልቁ በተባለው የአውሮፓ ወረራ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እስከ 200 ሺህ የሚገመቱ ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን ልከዋል።
በዚህ ጦርነት ቢያንስ 7 ሺህ 199 ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች ደግሞ የሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምቱን አስቀምጧል።
ከዚህ በተጨማሪም ሩሲያ እና ዩክሬን እያንዳንዳንቸው ቢያንስ 100 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮቻቸው መሞታቸውን ወይም መቁሰላቸውን የአሜሪካ ጦር ኃይል አስታውቋል።
ይህ ጦርነት ከ13 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ወደ ውጭ አገራትና በዩክሬን ውስጥ ተፈናቃይ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
በአንድ ወቅት በአንድ ሃገር ጥላ ስር የነበረችውን ዩክሬንን እየጨመረ ከመጣው ወታደራዊነትና የናዚ ርዕዮተ ዓለም የማላቀቅ ወታደራዊ ዘመቻ ነው ትላላች ሩሲያ ጦርነቱን። ዩክሬን እና አጋሮቿ በበኩላቸው ይህንን የሚያጣጥሉ ሲሆን ወረራም ነው ሲሉ ይጠሩታል።
“ወረራው የጋራ ህሊናችንን የጎዳ ነው” በማለት ለጠቅላላ ጉባኤው የተናገሩት ጉተሬዝ የተባባሩት መንግሥታትን ቻርተር እንዲሁም የዓለም አቀፍ ህግንም የጣሰ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
እየከረረ ያለው ጦርነት ሊያስከትለው የሚችለውን መዘዝም ግልጽ እና ወቅታቂ አደጋ ነው ብለውታል።
“አካባቢያዊ አለመረጋጋትን በማባባስ ዓለም አቀፍ ውጥረቶች እና መከፈፈሎች እንዲጨምሩ አድርጓል። በዓለማችን ላይ እየተከሰቱ ካሉ ቀውሶችና አንገብጋቢ ጉዳዮችም ትኩረት እንዳንሰጥና ፊታችንን እንድናዞር አደርጎናል” በማለት ጦርነቱ ያደረሰውን ጉዳት አስረድተዋል።
ስልሳ ሃገራት የውሳኔ ሃሳቡን የደገፉ ሲሆን በዚህም መሰረት “በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር መርህ መሰረት በተቻለ ፍጥነት በዩክሬን ሁሉን አቀፍ ፣ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም መድረስ አለበት” የሚል ሃሳብንም ይዟል።