ኡጋንዳዊቷ አትሌት በቀድሞ ፍቅረኛዋ ቤንዚን ተረጭቶባት በእሳት ተቃጠለች

አትሌት ሬቤካ ቼፕቴጋይ

የፎቶው ባለመብት, Uganda Athletics Federation/X

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ሬቤካ ቼፕቴጋይ

ኡጋንዳዊቷ አትሌት ሬቤካ ቼፕቴጋይ በቀድሞ ፍቅረኛዋ ቤንዚን ተረጭቶባት በእሳት ከተቃጠለች በኋላ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት ሆስፒታል ገባች።

በቅርቡ በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ አገሯን ወክላ በማራቶን ውድድር የተሳተፈችው የ33 ዓመቷ ቼፕቴታይ፤ 75 በመቶ የሚሆነው የሰውነት አካሏ መቃጠሉን ፖሊስ አስታውቋል።

አትሌቷ በቀድሞ ፍቅረኛዋ ጥቃቱ የተፈጸመባት መኖሪያዋ እና መለማመጃ ባደረገችባት ምዕራባዊ ኬንያ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ነው። የኬንያ ፖሊስ እንዳለው የቀድሞ ፍቅረኛ አትሌቷ ላይ ቤንዚን ረጭቶ እሳት መለኮሱን የዓይን እማኞች ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ቼፕቴጋይ ሕይወቷ የተረፈው ጎረቤቶቿ እሳቱን አጥፍተው በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ስለወሰዷት ነው።

የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ጄሬሚያ ኦሌ ኮሲኦም ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ ጥቃት አድራሹም ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶበታል ብለዋል።

ሁለቱም ሰዎች በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ኬንያ ኤልዶሬት ከተማ በሚገኘው ሞይ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ነው።

“ሁለቱ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ውጪ ሲጨቃጨቁ ታይተዋል። በጭቅጭቃቸው መካከል የቀድሞ ፍቅረኛ አትሌቷን ከማቃጠሉ በፊት ፈሳሽ ነገር ሲደፋባት ታይቷል” ብለዋል የፖሊስ ኃላፊው።

ከኬንያ ድንበር አዋስኝ በሆነችው የኡጋንዳ መንደር የተወለደችው ቼፕቴጋይ መኖሪያ እና የልምምድ ማዕከል ባደረገቻት አስተኛ የኬንያ ከተማ ቤተ ገንብታ ስትኖር ቆይታለች።

የአካባቢው ባለስልጣናት አትሌቷ እና የቀድሞ ፍቅረኛዋ በመሬት ይገባኛል ሲወዛገቡ ቆይተዋል። ፖሊስ በበኩሉ የወንጀል ምርመራውን እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

በፓሪሱ ኦሊምፒክ 44ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ቼፕቴጋይ እአአ በ2022 በታይላንድ በተካሄደ ውድድር አሸናፊ ነበረች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኬንያ ሴት አትሌቶችን ዒላማ የሚያደርጉ ጥቃቶች መበራከታቸው አሳሳቢ ሆኗል።

እአአ 2022 ላይ ዳማሪስ ሙቱአ የተባለች አትሌት በምዕራብ ኬንያ በምትገኘው ኢቴን ከተማ በትራስ ታፍና ተገድላ ነበር። ከዚህች አትሌት ግድያ ስድስት ወራት ቀደም ብሎ ደግሞ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በ5ሺህ ሜትር 4ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው አግነስ ቲሮፕ እንዲሁ በዚሁ ከተማ መገደሏ በርካቶችን ያስቆጣ ዜና ነበር።