ኬቲ ፔሪን ጨምሮ ሁሉም ሴቶች የሆኑበት ቡድን ወደ ሕዋ ሊያቀና ነው

ድምጻዊቷ ኬቲ ፔሪን ጨምሮ ወደ ሕዋ የሚያቀኑት ስድስት ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Blue Origin

የምስሉ መግለጫ, ድምጻዊቷ ኬቲ ፔሪን ጨምሮ ወደ ሕዋ የሚያቀኑት ስድስት ሴቶች

ድምጻዊቷ ኬቲ ፔሪን ጨምሮ ስድስት ሴቶች ወደ ሕዋ ሊያቀኑ ነው።

በቢልየነሩ ጄፍ ቤዞስ የሕዋ ቱሪዝም ሮኬት ወደ ሕዋ ከሚያቀኑት መካከል የጄፍ ቤዞስ እጮኛ እና የሲቢኤስ ፕሮግራም አቅራቢ ጌል ኪንግ ትገኝበታለች።

ኒው ሼፐርድ የተባለው ሮኬት ከቴክሳስ አሜሪካ ይነሳል። ጉዞው 11 ደቂቃ ይወስዳል። 100 ኪሎሜትር ከምድር በላይ የሚጓዙም ይሆናል።

በጉዞው ላይ ሳይንቲስቷ አይሻ ቦው፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ አማንዳ ንጋዩን እና ፕሮዲውሰሯ ኬሪን ፍሊን ይገኙበታል።

ሮኬቱ በራሱ የሚበር ስለሆነ አብራሪ አያስፈልገውም። ወደ ምድር የሚመለሰውም በፓራሹት ታግዞ ነው።

"ሁሉም ሴቶች የሆኑበት ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዋ ሲጓዝ እኔም አብሬ እንደምሄድ አስቤ አላውቅም ነበር። ያደግኩት ብዙ ነገር ኖሮኝ አይደለም። አሁን ዓለምን ሳይ እደነቃለሁ" ብላለት ኬቲ ፔሪ።

ብሉ ኦሪጅን የተባለው የጄፍ ቤዞስ ተቋም እንዳለው ለመጨረሻ ጊዜ ሴቶች ብቻ የተሳተፉበት የሕዋ ጉዞ የተከናወነው ከ60 ዓመት በፊት በሶቪየት ኅብረት ነበር።

ያኔም የተጓዘችው ቫለንቲና ትሬሽኮቫ ብቻዋን ነበር።

ኬቲ ፔሪ ለሕዋ ጉዞዋ ልምምድ ስታደርግ ቪድዮዎች ስትለቅ ነበር።

ብሉ ኦሪጅን የሕዋ ቱሪዝም 150,000 ዶላር እንደሚያስከፍል አስታውቋል።

ድርጅቱ ከሕዋ ቱሪዝም ጎን ለጎን የሕዋ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይም ይሠራል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኒው ሼፐርድ የተባለው ሮኬት በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ከእያንዳንዱ ጉዞ በኋላ ለቀጣዩ ዝግጁ ስለሚሆን የሚጠይቀውን ወጪ መቀነስ ይቻላል።

የአሜሪካ ሕግ ጠፈርተኞች ሥልጠና ወስደው እንዲጓዙ ያስገድዳል።

የኒው ሼፐርድ ተጓዥ የሆኑት ስድስት ሴቶች ከሁለት ቀናት በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና በዜሮ ስበት ከባቢ ውስጥ የመንቀሳቀስ ሥልጠና ወስደዋል።

ሁለት ሰዎች በጉዞው ድጋፍ ለመስጠት አብረዋቸው ይጓዛሉ።

የግል ተቋማት በሕዋ ቱሪዝም መግባት የከባቢ አየር ብክለት እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር ብራየን ኮክስ በበኩላው የሰው ልጆች ስልጣኔ ከመሬት ባሻገር ሕዋንም ያማከለ መሆን አለበት ይላሉ።

የአትሞስፌር ኬምስትሪ ባለሙያ ፕሮፌሰር ኤሉዊስ ማሪስ በበኩላቸው፣ ናይትሮጅንን ወደ ናይትሮጅን ኦክሳይድ የሚለውጠው ጉዞ ዓለም ከመጠን በላይ እንድትግል የሚያደርገውን ግሪን ሐውስ ጋዝ መጠን የሚጨምር ነው ይላሉ።

"የከባቢ አየርን ኬምስትሪ ያዛባል። የኦዞን ሽፋንን ያሳሳል። ከባቢ አየርን የሚጎዳ ደመና እንዲፈጠርም ያደርጋል" ሲሉም ያስረዳሉ።

ብዙ ሮኬት ከምድር በተወነጨፈ ቁጥር የኦዞን ሽፋን እንደሚሳሳ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የሕዋ ቱሪዝም እጅግ ውድ ስለሆለ ለብዙዎች ተደራሽ አይደለም።

"ብዙዎች እንቁላል መግዛት አቅቷቸዋል። የሕዋ ቱሪዝም የሚታሰብ አይደለም" ስትል ተዋናይቷ ኢሊቪያ ሙን ተችታለች።

የሕዋ ተመራማሪው ቲም ፒክ በበኩሉ ሰዎች ሕዋን መጎብኘታቸው ስለ አየር ንብረት ለውጥ መረጃ መስጠትን ጨምሮ አወንታዊ ውጤት ይኖረዋል ሲል ይከራከራል።

"የሕዋን ሳይንስ ተጠቅሞ የምድራችንን ሕይወት ማሻሻልን እደግፋለሁ። የሕዋ ጉዞ ችላ ሲባል አዝናለሁ" ሲል በግላስጎው በተካሄደው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ26 ላይ ተናግሯል።