የኤርትራ ባለሥልጣናት የወንጌል አማኞችን እያሰሩ መሆናቸው ተነገረ

የኤርትራ መንግሥት የፀጥታ ባለሥልጣናት በአገሪቱ ያሉ ወንጌላውያንን ከመኖሪያ ቤታቸው እየወሰዱ በማሰር ላይ መሆናቸው ተነገረ።

በተለይ ባለፉት ሳምንታት በሰሜናዊ ቀይ ባሕር፣ በአንሰባ እና በጋሽ ባርካ ዞኖች ውስጥ በርካታ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው መወሰዳቸው ቤተሰቦች እና የዕምነት መብት ተሟጋች ቡድን ገልጸዋል።

አዲሱ የእስር ዘመቻ በተለይ በዞኖቹ ምዕመናንን ላይ ብቻ ሳይሆን በአገልጋዮች ላይ ጭምር ያነጣጠረ ስለመሆኑ በቁጥጥር ስር ለሚገኙ ምዕመናን መብት የሚሟገተው ሪሊዝ ኤሪትሪያ የተባለው ቡድን ለቢቢሲ ገልጿል።

ባለፈው ወር በተለይ በተሰነይ፣ በአቁርደት እና በባረንቱ ከተሞች በርካታ ወንጌላውያን በአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።

በጋሽ ባርካ ዞን ከታሰሩት መካከል ከ60 በላይ የሚሆኑት ቢንቢና ተብላ በምትጠራ ከተማ በተከፈተ አዲስ የማቆያ እስር ቤት እንደሚገኙ የመብት ተቆርቋሪዎች ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በአዲ-ተከለዛን፣ ከረን እና ጋህተላይ ከተሞች ጭምር ብዙ ምዕመናን እንደታሰሩም ተገልጿል።

በኤርትራ መንግሥት ዕውቅና ከተሰጣቸው እምነቶች ውጪ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእስር ላይ ይገኛሉ።

በዚህ ወር በርካታ ሰዎች በእምነታቸው ምክንያት መታሰራቸው ለቢቢሲ ያረጋገጡት ‘ሪሊዝ ኤሪትሪያ’ የተባለውን የወንጌላውያን መብት ተሟጋች ድርጅት ዳይሬክተር፤ በአገሪቱ ያሉ መደበኛ ያልሆኑ እስር ቤቶች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።

የሪሊዝ ኤሪቲሪያ ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃነ አስመለሽ ከሳምንታት በፊት ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ “የወንጌላውያን ሁኔታ ባለፉት 20 ዓመታት መሻሻል አላሳየም። ቀደም ሲል የታሰሩት መሪዎች አሁን 20 ዓመት ሞልቷቸዋል።”

“ማንም የተከሰሰ ወይም ሕጋዊ የክስ ሂደት ተከትሎ የታሰረ ሰው የለም” ብለዋል።

የኤርትራ ባለሥልጣናት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ስለሚያዟቸው ዜጎች ይፋዊ መግለጫም ሆነ መረጃ አይሰጡም። ብዙውን ጊዜ በቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኙ አይፈቅዱም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው የካቲት ወር ባደረገው ጥሪ የኤርትራ ባለሥልጣናት በሕገ ወጥ መንገድ ያሰሩዋቸውን በሙሉ እንዲፈቱ እና ያሉበት ቦታ እና የጤና ሁኔታቸው ላይ መረጃ እንዲሰጡ ጠይቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክትል ዋና ኃላፊ ኢልሴ ብራንድስ ኬህሪስ ባለፈው የካቲት ወር በጄኔቫ ስዊትዘርላንድ ባደረጉት ስብሰባ በኤርትራ “ሰቃይ እና ሕገ-ወጥ እስር” ቀጥሏል ብለዋል።

“በሺህ የሚቆጠሩ የሃይማኖት ቡድኖች መሪዎች እና አባላት፣ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች ከገደብ የለሹ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት አምልጠው ይሰደዳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

የኤርትራ ባለሥልጣናት ግን ክሱን የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ “ፖለቲካዊ እና ኃላፊነት የጎደላቸው ውንጀላዎች” ሲሉ ያጣጥሉታል።

በአገሪቱ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ የመንግሥት ፍቃድ የተሰጣቸው የእምነት ተቋማት እንኳ ከመንግሥት ጣልቃገብነት ነፃ አይደሉም።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኤርትራ ባለሥልጣናት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚተዳደሩትን የጤና እና የትምህርት ተቋማትን በመዝጋት ጳጳስን እስከ ማሰር ደርሰው ነበር።

የኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ ትልቁ በሆነውና ብዙ አማኞች እንዳሉበት በሚነገረው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የውስጥ ጉዳዩ ጣልቃ በመግባት ፓትርያርኩን ከመሪነት በማንሳት ለዓመታት በቁም እስራት እንዲቆይ አድርጓል የሚል ክስ ይቀርብበታል።

በመሪዋ ሞት ምክንያት ፓትርያርክ አጥታ የቆየችው ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት በውጭ አገር በሚገኙ ተከታዮች ተከፋፍላለች።

ከነጻነት ጀምሮ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ መምህራን እና ሼሆች ታስረዋል፣ ከታሰሩትም በርካቶች ደብዛቸው ጠፍተዋል ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።