የአሜሪካው አየር መንገድ እንደ ህጻን የቆጠራቸው የ101 ዓመቷ የዕድሜ ባለጸጋ

የአሜሪካው አየር መንገድ የ101 ዓመቷን የዕድሜ ባለጸጋ እድሜያቸውን እንደ አንድ ዓመት ህጻን በተደጋጋሚ አሳስቶባቸው ተቸግረዋል። እንዴት?
ስህተቱ የሚፈጠረው በበይነ መረብ [ኦንላይን] ቲኬት በሚገዛበት ወቅት ነው።
የዕድሜ ባለጸጋዋ የተወለዱት በአውሮፓውያኑ 1922 ነው ነገር ግን የአየር መንገዱ የኮምፒውተር ሥርዓት በዚህ ወቅት ላይወለዱ ይችላሉ በሚል ግምት የትውልድ ጊዜያቸውን 2022 አድርጎ ይሞላዋል።
በቅርቡም ጉዟቸውን ሊያደርጉ በአየር ማረፊያው በደረሱበት ወቅት የተፈጠረውን ግርምት እና ሳቅን ቢቢሲ ተመልክቷል።
“ትንሽ ልጅ ናት ብለው አስበው ስደርስ የእድሜ ባለጸጋ ሆነው ሲያገኙኝ በጣም አስቂኝ ነው እንጂ” ይላሉ።
ይህ የቅርቡ ክስተት የተፈጠረው የቢቢሲ ዘጋቢ በመንገደኝነት በተሳፈረበት ከቺካጎ ወደ ማርኬት ከተማ በነበረው በረራ ላይ ነው።
ፓትሪሻ በወቅቱ ከልጃቸው ክሪስ ጋር እየተጓዙ ነበር።
“ልጄ ናት ቲኬቱን በኦንላይን የገዛችው እና የቲኬት ሥርዓቱን የሚቆጣጠረው ኮምፒውተር የተወለድኩበት ዓመት 1922 ሳይሆን 2022 ነው ሲል አስቦ ቀየረው። ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል እኔን የዕድሜ ባለጸጋ ሳይሆን ልጅ እንደሆንኩ አድርገው እየጠበቁ ነበር” ይላሉ።
ከህጻን ጋር በሚያሳስታቸው ኮምፒውተር ምክንያት የፓትሪሻ መቀመጫ ተይዞ ነበር።
ህጻን በመሆናቸው ይታቀፋሉ በሚል ይመስላል አንድ ትልቅ ሰው በእሳቸው ቦታ ላይ ሙሉ ክፍያውን ፈጽሞ ተቀምጦበታል።
የአየር ማረፊያው የኮምፒውተር ሥርዓት ዕድሜ 100 ዓመት እና ከዚያ በታች ብቻ እንዲመዘግብ በመደረጉ እንደ ፓትሪሺያ ያሉ ከምዕተ ዓመት ያለፉ የዕድሜ ባለጸጋን መመዝገብ ተስኖታል።
የቀድሞዋ ነርስ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ እና ከቀዝቃዛው ክረምት ለማምለጥ በየዓመቱ በረራዎችን ያደርጋሉ። ነገር ግን በቅርቡ ሁለት ጊዜ ሲሄዱም ሆነ ሲመለሱ ይህ ግራ መጋባት የገጠማቸው ቢሆንም የአሜሪካ የአየር መንገድ ሠራተኞች ደግ እና አጋዥ ነበሩ ይላሉ።
የአሜሪካ አየር መንገድ የፓትሪሻን የዕድሜ ግራ መጋባት አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
ምንም እንኳን ሁኔታው ፈገግ ቢያስብላቸውም በዓለማችን ላይ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የኖሩት ፓትሪሺያ ለወደፊቱ አንዳንድ እክሎች ስለሚፈጥሩ ችግሩ እንዲስተካከል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ለምሳሌ የአየር ማረፊያ ሠራተኞች ሊታቀፍ የሚችል ህጻን ስለሚጠብቁ እሳቸውን ሊያግዝ የሚችል ትራንስፖርት የላቸውም።
ከዚህ ቀደም በነበረው በረራቸው ፓትሪሺያ እና ልጃቸው ሌሎች ተሳፋሪዎች ከወረዱ በኋላ በአውሮፕላኑ ውስጥ እየተጠባበቁ ነበር ምክንያቱም ሠራተኞች ዊልቸር ስላላዘጋጁላቸው።
የእርሳቸው ትክክለኛ ዕድሜ በአየር መንገዱ እና ማረፊያዎቹ ዕውቅና መሰጠቱ ለልጃቸው ክሪስም ጠቃሚ ነው።
“ምስኪን ልጄ ሻንጣችን እና ሌሎች ዕቃዎችንን ተሸክማ ርቀት ካለው ከአንዱ መግቢያ ወደ ሌላኛው መግቢያ ትንከራታለች። ስለዚህ የኮምፒውተር ሥርዓታቸውን እንዲያስተካክሉ እፈልጋለሁ” ይላሉ።
ፓትሪሺያ እስከ 97 ዓመታቸው ድረስ ብቻቸውን ይበሩ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ለመጓዝ በቤተሰቦቻቸው እርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው።
“አሁን በዐይኔ ዕይታ ላይ የተወሰነ ችግር ስላጋጠመኝ በራሴ በረራ ማድረግ አልፈልግም” ሲሉ ፓትሪሺያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን ይህ ችግር እንኳን ባይቀረፍ ከመብረር እንደማያስቀራቸው አጽንኦት በመስጠት ይናገራሉ።
በሚቀጥለው የመጸው ወቅትም በረራ ለማድረግ አቅደዋል። በዚያን ወቅት 102 ዓመት የሚሞላቸው ሲሆን፣ በዚያን ጊዜ የአየር መንገዱ ኮምፒውተሮች ትክከለኛ ዕድሜያቸውን የመመዝገብ ሥርዓት ሊያዳብሩ ይችሉ ይሆናል።












