“ቤታችንን በላያችን ላይ ቢያፈርሱትም የትውልድ ቀያችንን አንለቅም” የጋዛ ቤተሰቦች

እስራኤል ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎችን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ አስገዳጅ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።

ማስጠንቀቂያውን የሰሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩም ወደ ደቡባዊ ጋዛ እየጎረፉ ነው።

ወደ ደቡባዊ ጋዛ እየተጓዙ የነበሩ ፍልስጥኤማውያንም በእስራኤል የአየር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

እስራኤል ላለፉት አስር ቀናት ቀን ተሌት ጋዛን በቦምብ በመደብደብ ላይ ትገኛለች።

ምናልባትም በቀጣይ ቀናት እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዝ ልታስገባ ትችላለች ተብሎ ይጠበቃል።

እግረኛ ጦር ቢገባም ቤታችንን፣ ቀያችንን አንለቅም ያሉ የጋዛ ነዋሪዎች ግን አልታጡም።

“ትውልድ አገሬን ለቅቄ አልሄድም፣ በጭራሽ አልወጣም” ሲልም የ42 ዓመቱ መሐመድ ኢብራሂም ተናግሯል።

ለቢቢሲ አረብኛ በደረሰው ቪዲዮ ላይ በእነመሐመድ የተጨናነቀች ሳሎን ውስጥ ዘመድ አዝማድ ከበው ተቀምጠው ይታያሉ። አንዳንዶች ያወራሉ፣ ሌሎች ደግሞ ስልካቸውን ያያሉ።

“ቤታችንን በላያችን ላይ ሊያፈርሱት ቢሆንም እንኳን ቀያችንን ትተን ወደሌላ ቦታ አንሸሽም። እዚሁ እቆያለሁ” ሲል መሐመድ አክሏል።

ከአስር ቀናት በፊት ሐማስ በወሰደው ያልተጠበቀ ወታደራዊ እርምጃ 1ሺህ 400 ሰዎች በእስራኤል ተገድለዋል።

የሐማስ ታጣቂዎች በጋዛ ሰርጥ በኩል ድንበር ተሻግረው ነበር በንጹሐን እና በወታደሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙት።

በሺዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ወታደሮች ከጠቅላይ ሚኒስትራቸው ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ሆነው “ሐማስን ለማጥፋት” ዝተዋል።

እስራኤል ቀን ተሌት እየፈጸመችው ካለው የአየር ጥቃት ለማምለጥም መሐመድ ከቤተሰቦቹ ጋር ሆኖ በጋዛ ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች በድጋሚ ተዘዋውረዋል።

“ባለፈው እሁድ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ የአየር ጥቃቶች እና ሮኬቶች ተወነጨፉብን። ከባለቤቴ እና ከአራት ልጆቼ ጋር ቤታችንን ለቀን ወጣን” ይላል።

ቤተሰቡ በሰሜን ጃባሊያ የሚገኘውን ቤታቸውን ለቀው ወደ ምሥራቃዊ ጋዛ አቀኑ። ነገር ግን ያ አካባቢም ከአየር ጥቃቱ እንደማይተርፍ ሲሰሙ ወደ ሰሜን ተመለሱ።

በአሁኑ ወቅት በሰሜናዊ ጋዛ በዘመዶቻቸው የጋራ መኖሪያ ቤት ተጨናንቀው ይገኛሉ። ልጆቹ ግቢያቸው፣ የአትክልት ቦታቸው እንደናፈቃቸው ይናገራል።

ልጁ አህመድ ጓደኛው ጋር ባለመገናኘቱ በሕይወት አለ ወይ እያለ ይጠይቃል።

እስራኤል ሐማስን ሰላማዊ ሰዎችን እንደ ከለላ በመጠቀም እና በመሠረተ ልማቶች ውስጥ በመደበቅ ትከሰዋለች። ሐማስ ግን ይህንን አይቀበልም።

እስራኤል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎችን ከቀያቸው እንዲወጡ አስገዳጅ ትዕዛዝ ያስተላለፈች ሲሆን፣ የዓለም የጤና ድርጅት ህሙማንን ከሆስፒታል ውጡ ማለት “የሞት ፍርድ ነው” ሲልም አሳስቧል።

በባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ፍልስጥኤማውያን ቤታቸውን ለቀው ተፈናቅለዋል።

መሐመድ ምንም አማራጭ ስላልታየው ባለበት እንደሚቆይም ተናግሯል።

“ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንድንሰደድ እየተነገረን ነው፤ እኔ እና ቤተሰቤ የት እንሂድ?” ሲልም ይጠይቃል።

“ወደ ደቡባዊ ጋዛ የሚሰደዱ ሁሉ ስህተት እየፈጸሙ ነው” የሚለው ሌላኛው ነዋሪ ፋይዝ ኤልታኒ እና ቤተሰቦቹ ከሰሜን ጋዛ ወጥተው ከተሰደዱ ተመልሰው ለመምጣት በጭራሽ እንደማይፈቀድላቸው እንደሚሰጋ ተናግሯል።

የ38 ዓመቱ የግንባታ ሠራተኛ አቦ ጃሚኤል ከውሃ ጉድጓድ ውስጥ የመጨረሻውን የውሃ ጠብታ ለማግኘት አጎንብሷል።

እስራኤል ጋዛ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ከበባ እንዲደረግ ያዘዘች ሲሆን፣ በጋዛ ኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ነዳጅ አይኖርም ሲሉ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ባለፈው ሳምንት ትዕዛዝ ሰጥተዋል። እስራኤል በሐማስ የታገቱ ግለሰቦች እንዲለቀቁም ቅድመ ሁኔታ አቅርባለች።

ጋዛ ሰርጥ ወደ 2.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጥኤማውያን መኖሪያ ስትሆን ለ16 ዓመታት ያህል በቆየ ከበባ ውስጥ ትገኛለች።

“ለስምንት ቀናት ምግብም ሆነ ውሃ የለም፣ መብራት የለም፣ ሕይወት የለም ሁኔታው በሰቆቃ የተሞላ ነው” ሲል አቦ ጃሚል ምሬቱን ተናግሯል።

ሁለት ወንድ እና ሦስት ሴት ልጆች አሉት። የመጨረሻው ልጁ አራት ዓመቱ ቢሆንም ቤታቸውን ለቀው መሰደድን እንደ አማራጭ አያዩትም።

እስራኤል ለአስር ቀናት በጋዛ እየፈጸመችው ባለችው የማያባራ የአየር ጥቃት ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል።

“የምንሄድበት ቦታ የለንም። ቤታችንን በአየር ቢያጠቁትም አንወጣም” ሲል አቦ ጃሚል ይናገራል።

“አምስት፣ ስድስት ቤተሰቦች ይዘን ወደየትስ መሄድ እንችላለን?” አቦ ጃሚል ይጠይቃል።

በማያባራ የአየር ጥቃት ስር ባለችው ጋዛ ሰርጥ ያሉ ህጻናት ትንሽ ጋብ ሲል ወደ ጎዳናዎች ላይ ወጥተው ይጫወታሉ።

የሕጻን ነገር አደጋውን ረስተው መንገዶች ላይ ይሯሯጣሉ።

የጦርነቱ ማዕከል በሆነችው እና በጥቃት እየተናጠች ባለችው ጋዛም ትንሽ እረፍት መገኘቱም እፎይታ ነው።

ከጋዛ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ ከ18 ዓመት በታች ናቸው። በአሁኑ አየር ጥቃቶችም 700 ሕጻናት መገደላቸውን የፍልስጥኤም ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ እግረኛ ጦሯን የምታስገባ ከሆነ እና የሐማስ ተዋጊዎችም በሕንጻዎች እና ዋሻዎች ላይ ሽምቅ ውጊያ የሚያካሂዱ ከሆነ ጦርነቱ ለወራት የሚቀጥል እና የከፋ ውድመትም ያስከትላል ተብሏል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ዋጋ የሚከፍሉ ይሆናል።