ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሐማስን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ የጦር መርከቦቿን ወደ እስራኤል አስጠጋች
አሜሪካ የአውሮፕላን ተሸካሚዎችን፣ የጦር መርከቦችን እና ጄቶች ወደ ምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን ባህር እያስጠጋች መሆኑን ገለጠች።
ለእስራኤል ተጨማሪ መሳሪያዎችን እና ጥይቶችን እንደምትሰጥም አስታውቃለች።
አሜሪካ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ሐማስ በደቡብ እስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ሲሆን ፕሬዝዳንት ባይደን ጥቃቱን “ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅና አሰቃቂ” ሲሉ ጠርተውታል።
አሜሪካ ዜጎቿ ስለመገደላቸው እና በምርኮ ከተወሰዱት መካከል ስለመኖራቸውን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።
ከ700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና 100 ሰዎች መታገታቸውን እስራኤል ገልጻለች።
የፍልስጤም ባለስልጣናት በበኩላቸው የእስራኤል የአየር ጥቃትን ተከትሎ በጋዛ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን እንዳሉት የአገሪቱ አውሮፕላን ተሸካሚ፣ ሚሳይል ማስወንጨፊያ እና አራት ጸረ ሚሳይሎችም ወደ አካባቢው እያመሩ ነው። የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶችም ይላካሉ ተብሏል።
ለእሥራኤል ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ በሚቀጥሉት ቀናት እንደሚላክ ኋይት ሐውስ ገልጾ፣ የእስራኤል ጠላቶች አጋጣሚውን ለመጠቀም እንዳይሞክሩ አሜሪካ እየሠራችም ነው ብሏል።
የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ የሐማስን ጥቃት እንደሚደግፉ ገልጸው እስራኤል በቀጠናው ወደ አደጋ በመክተት ተጠያቂ መሆን አለባት ብለዋል።
ከኢራን ያገኘው እርዳታ ጥቃቱን ለመፈጸም እንደረዳው ሐማስ ተናግሯል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው የኢራንን በቀጥታ መሳተፍ አሜሪካ በማስረጃ አለማረጋገጧን ቢጠቅሱም ቴህራን መቀመጫውን በጋዛ ያደረገውን ቡድን ለዓመታት ስትረዳ መቆየቷ ይታወቃል።
"ከኢራን ለብዙ ዓመታት ካገኘው ድጋፍ ውጭ ሐማስ ሐማስን አይሆንም ነበር። ከዚህ ጥቃት ጀርባ ኢራን እንደነበረች ወይም ተሳታፊ እንደነበረች የሚጠቁም ማስረጃ እስካሁን አላገኘንም። ለብዙ ዓመታት የተደረገው ድጋፍ ግን ግልፅ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት በእስራኤል ላይ በደረሰው ጥቃት እጇ እንደሌለባት ኢራን መናገሯን ሮይተርስ ዘግቧል።
ብሊንከን አክለውም በጥቃቱ የአሜሪካ ዜጎች ስለመጎዳታቸው የሚገልጹ ዘገባዎችን ባለስልጣናት እየመረመሩ ነው ብለዋል።
"ከሟቾቹ መካከል በርካታ አሜሪካውያን እንዳሉ ሪፖርቶች አግኝተናል። ሪፖርቶቹን ለማረጋገጥ ጠንክረን እየሠራን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ዩክሬን እና ታይላንድን ጨምሮ የሌሎች ሃገራትም ዜጎቻቸው መሞታቸውን ሪፖርት አድርገዋል።
"የእስራኤል ሠላማዊ ዜጎችን በየከተማቸው፣ በቤታቸው በጥይት እየገደሉ እና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በጋዛ ድንበር ላይ የተጎተቱበት ከባድ የሽብር ጥቃት ነው።” ብለዋል።
"ይህ በመላው እስራኤል ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መገመት ትችላላችሁ። ዓለም ያየውን ነገር ማውገዝ አለበት።"
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጠፍተዋል አሁን ድረስ የገቡበት አልታወቀም።
ከእነዚህም መካከል የ23 ዓመቱ አሜሪካዊ-እስራኤላዊ ሄርሽ ጎልበርግ-ፖሊን አንዱ ሲሆን ታጣቂዎቹ ጥቃት ባደረሱበት የበረሃ የሙዚቃ ድግስ ላይ እየተሳተፈ ነበር። ወላጆቹ ለእየሩሳሌም ፖስት እንደተናገሩት “እወዳችኋለሁ” እና “ይቅርታ” የሚሉ ሁለት መልዕክቶችን ልኮላቸዋል።
በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር ማይክል ሄርዞግ ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት በደቡባዊ እስራኤል ከታፈኑት ወታደሮች እና ሲቪሎች መካከል አሜሪካውያን መኖራቸውን ቢገልጹም ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
አሜሪካ ለቅርብ አጋሯ እስራኤል በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያወጣ ወታደራዊ እርዳታ ትልካለች። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እስራኤል ከፍተኛውን የአሜሪካ ዕርዳታ የምታገኝ ሃገር ነች።
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና በጋዛ ስላለው ሁኔታ ለመወያየት በኒውዮርክ እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል።