ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አልጀዚራ የጋዜጠኛውን ግድያ ወደ አለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ወሰደ
አልጀዚራ የጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አቅላን ግድያ ወደ አለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ወሰደ።
የሚዲያ ተቋሙ ክሱን ያቀረበውም ሆን ብለው ገድለዋታል ባለው የእስራኤል ኃይል ነው።
ፍልስጥኤማዊቷ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለችው ዌስት ባንክ ጦሩ ባደረሰው ጥቃት ጭንቅላቷ በጥይት ተመትቶም ነው የተገደለችው።
የእስራኤል ጦር ጋዜጠኛዋን የገደለው በግንቦት ወር ነበር።
የእስራኤል ጦር ከወታደሮቹ አንዱ ገድሏት ሊሆን እንደሚችል ገልጾ ነገር ግን ሞቷ የታቀደበት አይደለም ሲል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
አልጀዚራ በበኩሉ የእስራኤልን መደምደሚያ መሰረ ቢስ ነው ሲል አጣጥሎታል።
ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ሆን ተብሎ ታቅዶ የተፈጸመ ግድያ ነው ብሏል የሚዲያ ተቋሙ።
“የትኛውም ሰው ሆነ ማንኛውም አካል የእስራኤል መከላከያ ሰራዊትንም ሆነ ወታደሮችን አይመረምርም፤ ማንም ሰው ስለ ጦርነት ሥነ ምግባር አይሰብከንም፤ ጭራሽ አልጀዚራ የማይሆን ነው” ሲሉ ተሰናባቹ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ ተናግረዋል።
እስራኤል የአይሲሲን ስልጣን የማትቀበል ሲሆን በሄግ ተቀማጭነቱን ያደረገው ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ግዛቶች ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ የጦር ወንጀሎችን ለመመርመር ቢጠይቅም ለመተባበር ፈቃደኛ አልሆነችም።
የ51 ዓመቷ ሺሪን አቡ አቅላ የእስራኤል ጦር በጄኒን የስደተኞች ካምፕ ያደረገውን ከበባና ጥቃት ለአልጀዚራ የአረብኛ ፕሮግራም ለመዘገብም ነበር ወደ ስፍራው ያቀናችው።
በስፍራው ላይ እያለች በእስራኤል ወታደሮችና በፍልስጥኤም ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መከፈቱ ተዘግቧል።
በወቅቱ የጥይት መከላከያ ኮፍያ (ሄልሜት) እንዲሁም ፕሬስ የሚል የተለጠፈበት ሰማያዊ ጃኬት ለብሳ ነበር። በስፍራው ሌሎች ጋዜጠኞች ጋር የነበረች ሲሆን ከሷ በተጨማሪም ሌላ ጋዜጠኛ በተተኮሰበት ጥይት ተገድሏል።
ጋዜጠኞች፣ የዓይን እማኞችና የፍልስጥኤም ባለስልጣናት የእስራኤል ወታደሮች እንደተኮሱባት የተናገሩ ሲሆን ይህንንም የተባበሩት መንግታት ድርጅትም አረጋግጫለሁ ብሏል።