ባይደን ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የአሜሪካውያን የትዳር አጋሮች ከአገር እንዳይባረሩ ሊያደርጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሕጋዊ ሰነድ ለሌላቸው የአሜሪካውያን የትዳር አጋሮች ከአገር እንዳይባረሩ የሚከለክል አዲስ ፖሊሲ ሊያውጁ መሆኑን ባለሥልጣናት ገለጹ።
ፖሊሲው ተፈጻሚ የሚሆነው ቢያንስ አስር ዓመታት በአሜሪካ ለኖሩ የትዳር አጋሮች ላይ ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ በሕጋዊ መንገድ እንዲሠሩ ያስችላቸዋል ተብሏል።
የኦባማ አስተዳደር ወደ አሜሪካ ብቻቸውን የሚገቡ ህጻናትን ለመጠበቅ ካወጀው ከአውሮፓውያኑ 2012 ፖሊሲያቸው ወዲህ ይህ የባይደን ውሳኔ ሰነድ አልባ ለሆኑ ስደተኞች ከለላ የሚሰጥ ነው ተብሎም ተወድሷል።
ዋይት ሐውስ ይህ ፖሊሲ ከ500 ሺህ በላይ የአሜሪካውያን የትዳር አጋሮቻቸውን ተጠቃሚ ያደርጋል ብሎ ያምናል።
ይህ ውሳኔ በተጨማሪም የአሜሪካ ዜግነት ካላቸው ጋር ጋብቻ የፈጸሙ ወላጆች ልጆችንም የሚመመለከት ይሆናል። ከ21 ዓመት በታች ያሉ 50 ሺህ ህጻናት እና ታዳጊዎች ይሄው ፖሊሲ ከለላ ይሰጣቸዋል።
ፕሬዚዳንት ባይደን የአገሪቱን የኢሚግሬሽን ሥርዓት “የበለጠ ፍትሃዊ እና አካታች” ለማድረግ በቅርቡ ቃል ገብተው ነበር።
ባይደን ይፋ ያደረጉት ፖሊሲ ከ530 ሺህ በላይ ብቻቸውን ወደ አሜሪካ ለመጡ ህጻናት ከለላ የሰጠው ‘ዳካ’ የተሰኘው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፕሮግራም 12ኛ ዓመቱ በሚከበርበት መባቻ ነው።
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ሰኞ ዕለት እንዳስታወቁት የአሜሪካ ዜግነት ካላቸው ጋር የተጋቡ እና በአገሪቱ ለአስር ዓመታት የኖሩ ግለሰቦች ከዚህ ፖሊሲ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
መስፈርቱን የሚያሟሉት የትዳር አጋሮች ለቋሚ ነዋሪነት ለማመልከት ሦስት ዓመት የሚኖራቸው ሲሆን፣ የሦስት ዓመት የሥራ ፈቃድም ይሰጣቸዋል።
ዋይት ሐውስ መስፈርቱን የሚያሟሉት አብዛኞቹ በአሜሪካ ውስጥ በአማካኝ ለ23 ዓመታት መኖራቸውን ያምናል። አብዛኞቹም በሜክሲኮ የተወለዱ መሆናቸውም ተገልጿል።
በኢሚግሬሽን ማሻሻያ ላይ የሚሠራ ‘ነምበር ዩኤስኤ’ የተሰኘ ቡድን አዲሱን ፖሊሲ “ምክንያታዊ ያልሆነ” ሲል ነቅፎታል።
“ፕሬዚዳንት ባይደን በታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋውን የድንበር ቀውስ ከመግታት ይልቅ መራጮችን እና በምክር ቤት ውስጥ የተመረጡ ተወካዮቻቸውን በማለፍ ኢሕገ መንግሥታዊ ሂደትን በመጠቀም ሥልጣናቸውን ተጠቅመዋል። በዚህም በሕገወጥ መንገድ አሜሪካ ውስጥ ለሚገቡ ሰዎች ምህረት ይደረጋል የሚለውን መልዕክት አስተላልፈዋል” ሲሉ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጄምስ ማሳ በሰጡት መግለጫ ተችተዋል።












