ፑቲን ከ24 ዓመታት በኋላ ሰሜን ኮሪያን ሊጎበኙ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከ24 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 11/2016 ሰሜን ኮሪያን ይጎበኛሉ።
ፑቲን በሰሜን ኮሪያ መዲና ፒዮንግያንግ የሀገሪቱን መሪ ኪም ጆንንግ ኡንን አግኝተው እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል።
ሁለቱ መሪዎች ባለፈው መስከረም ወር በሩስያ ተገናኝተው ነበር። ሆኖም ቭላድሚር ፑቲን ሰሜን ኮሪያን ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኙት ከ24 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ ሚሊኒየም (2000) ነበር።
አሜሪካ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እየጠበቀ መምጣት እንዳሳሰባት ስትገልጽ የፑቲን ቢሮ ክሬምሊን ደግሞ “የወዳጅ ሀገር ጉብኘት” ሲል ጠርቶታል።
በዚህ ጉብኝት ፑቲን እና ኪም የደህንነት ጉዳዮችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የትብብር ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙ እና የጋራ መግለጫ እንደሚሰጡ የሩስያ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።
ኪም ኢል ሳንግ አደባባይ ላይ ለፑቲን በወታደራዊ ትርኢት የታጀበ አቀባበል እንደሚደረግላቸውም ይጠበቃል።
ፑቲን በፒዮንግ ያንግ በሚገኘው ብቸኛው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ውስጥ በሚደረግ መርሃ ግብር ላይ እንደሚታደሙ እና እንደሚጎበኙትም ይጠበቃል።
ቭላድሚር ፑቲን ፒዮንግያንግ በሚገኘው ኩምሳን በተባለው የእንግዳ ማሪፊያ እንደሚቆዩ የሚገልጹ ሪፖርቶች ወጥተዋል። ይህንን የእንግዳ ማረፊያ ከ5 ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2019 የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ሀገሪቱን በጎበኙበት ወቅት አርፈውበታል።
ከፑቲን ጋር አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብረዋቸው ከሚጓዙት መካከል ናቸው።
የሩስያው መሪ ከጉብኝታቸው በፊት ሩስያ በዩክሬን እያደረገችው ባለው ጦርነት ፒዮንግያንግ እያደረገች ላለው “ጥብቅ ድጋፍ” አክብሮታቸውን መግለጻቸውን በሰሜን ኮሪያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨ ደብዳቤ ያመለክታል።
“በምዕራባውያን ቁጥጥር ውስጥ ያልሆነ” የደህንነት እና የንግድ ስርዓት ለመዘርጋትም ቃል መግባታቸውንም ይኼው ደብዳቤ ይሳያል።
በተጨማሪም ፑቲን ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ የሚደርስባትን ጫና እና ወታደራዊ ስጋት ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።
የሰሜን ኮሪያው ፒዮንግ ያንግ ባለፈው ሳምንት ከሩስያ ጋር ያለን ግንኙነት ወደማይሰበር ደረጃ ተሸጋግሯል ብለዋል።
ባለፈው መስከረም በሩስያ ሁለቱ መሪዎች ሲገናኙ ፑቲን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ወታደራዊ ትብብር ልንፈጽም የምንችልበት “ዕድል” አለ ሲሉ ኪም ደግሞ ሩስያ በዩክሬን እያደረገች ላለው ጦርነት “ድል”ን ተመኝተዋል።
አሜሪካ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየጠበቀ የመጣው ግንኙት እንዳሳሰባት ገልጻለች።
የሀገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቦይ በፑቲን “ጉብኝት ስጋት የለንም።
ስጋት ያለን ጥልቀቱ እየጨመረ በመጣው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ነው” ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2000 ፑቲን የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸውን ሲጀምሩ ወደ ሰሜን ኮሩያ አቅንተው የአሁኑን መሪ ኪም ጆንግ ኡን አባት ኪም ጆን ኢልን አግኘተው አነጋግረው ነበር።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ባለፉት ጥቂት አመታት እያደገ የመጣ ሲሆን በተለይ ሩስያ ዩክሬንን ስትወር ግንኙነታቸው ጠብቋል።
ሰሜን ኮሪያ የስለላ ሳተላይት ለማምጠቅ ሞክራ ባለመሳከቱ በዚህ ዘርፍ፣ በምግብ፣ በነዳጅ እና በውጪ ምንዛሬ እርዳታን ትሻለች።
ሩስያ በበኩሏ በዩክሬን ጦርነት የጦር መሳሪያዎች እጥረት እንደገጠማት ይነገራል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ፒዮንግያንግ ልዩ ልዩ መሳሪያዎችን ለሩስያ ታቀርባለች ሲሉ ይከሳሉ። ሰሜን ኮሪያ በምትኩ ከሩስያ የምግብ ድግፍ እንደሚደረግላት ይታመናል። ሆኖም ሁለቱም ሀገራት ይህንን መረጃ ሀሰት ነው ይላሉ።












