የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማጽያን ዋና ከተማዋን እስከሚቆጣጠሩ ድረስ እንደሚዋጉ ገለጹ

አማጽያኑ የጎማ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ገልጸዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በምስራቅ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቁልፍ ከተማ የሆነችውን ጎማን የያዙት የኮንጎ አማጽያን መዲናዋን ኬንሻሳን እስከሚቆጣጠሩ ድረስ በውጊያቸው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።

ኤም23ን የተሰኘውን ጨምሮ የአማጺያኑን ቡድኖች ጥምረት የሚመሩት ኮርኔይ ናንጋ እንዳሉት ከሆነ የመጨረሻ ዓላማቸው የፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲን መንግስት መጣል ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተኩስ ማቆም ጥሪ ቢደረግም በሩዋንዳ የሚደገፉት አማጽያን በማዕድን የበለጸገችውን ምስራቃዊቷን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ቡካቩን ለመቆጣጠር እየገሰገሱ ነው።

ጎማ በአማጽያኑ ስር ከወደቀች በኋላ ፕሬዝዳንት ቲሺሴኬዲ በቴሌቭዥን በተላለፈ ንግግራቸው ላይ "ጠንካራ እና የተቀናጀ ምላሽ" በመስጠት ከአማጽያኑ ግዛቱን መልሶ ለመውሰድ እየተሠራ ነው ብለዋል።

"አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን አለባችሁ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንድትዋረድ ወይም እንትሽመደመድ አንፈቅድም። እንዋጋለን እናሸንፋለን" ሲሉ ረቡዕ አመሻሽ ላይ ተናግረዋል።

ጦርነቱ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ ቀድሞ የነበረውን የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳባባሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።

ናንጋ አማጽያኑን የጎማ አዲሶቹ አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረው ኃላፊነቱን ተረክበው እንደሚሠሩ ሐሙስ ዕለት አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት ውጊያው ከተባባሰ ወዲህ በከተማዋ የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦት ተቋርጧል፤ የምግብ እጥረትም አለ።

"እስከ ኬንሻሳ ድረስ ያለውን የነጻነት ጉዞ እንቀጥላለን" ሲሉ ናንጋ አክለው ተናግረዋል።

አማጽያኑ አሁን ካሉበት ኬንሻሳ ያለው ርቀት 2 ሺህ 600 ኪሎሜትር መሆኑን ተከትሎ ተንታኞች ከሀገሪቱ ስፋት አንጻር ይህ ዓይነቱ ጥቃት የማይታሰብ ነው ብለዋል። ሆኖም በ1997 በሩዋንዳ የሚደገፉ ኃይሎች የረዥም ጊዜ መሪ የነበሩትን ሞቡቱ ሴሴ ሴኮን ከስልጣን ባባረሩበት ወቅት ይህንን ማሳካት ተችሏል።

ጎረቤት ሩዋንዳ አማጽያኑን ከመደገፍ ባለፈ ወታደሮቿም በጎማ እንዳሉ በመግለጽ ለምትከሰው ኬንሻሳ የናንጋ አስተያየት የበለጠ ቁጣን ይጨምራል።

ሩዋንዳ ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ብታደርግም ዓለም አቀፍ ትችት እየደረሰባት ነው።

በህብረቱ ውስጥ ዋነኛው አማጺ ቡድን የሆነው ኤም23 በቱትሲዎች የሚመራ ሲሆን በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚገኘውን አናሳ ቡድን መብት ለማስጠበቅ መሳሪያ አንስቻለሁ ብሏል።

የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ቱትሲ ሲሆኑ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት እአአ በ1994 በሩዋንዳ በተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ የሁቱ ታጣቂዎችን ረድቷል በሚልም ይከሳሉ።

በጎማ የውሃ አቅርቦት ተቋርጧል

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የደቡባዊ አፍሪካ አገራት ቡድን ሳድክ በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል የሠላም አስከባሪ ኃይል ቢኖራቸውም የአማጺውን ጥቃት ማስቆም አልቻሉም።

በግጭቱ ከበርካታ አገራት የተውጣጡ የሠላም አስከባሪዎች የተገደሉ ሲሆን 13 ወታደሮቿ የሞቱባት ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዳለች።

ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ ለሟቾቹ ተጠያቂዎች የኤም23 ተዋጊዎች እና የሩዋንዳ ጦር ናቸው ማለታቸውን ተከትሎ ካጋሜ ሩዋንዳ አስፈላጊ ከሆነ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለመፋለም ዝግጁ መሆኗን ረቡዕ ዕለት ገልጸዋል።

ካጋሜ በኤክስ ላይ በጠንካራ ቃላት በተሞላ መግለጫቸው ራማፎሳ ሁለቱ መሪዎች ያደረጉትን ንግግር አዛብተዋል ሲሉ ከሰዋል።

"ደቡብ አፍሪካ ለሠላማዊ መፍትሄዎች አስተዋፅኦ ማድረግ ከፈለገች ጥሩ ነው። ካልሆነ ግን ደቡብ አፍሪካ የሠላም አስከባሪ ወይም አስታራቂ ሚና ለመጫወት ምንም አይነት ብቃት አይኖራትም። እናም ደቡብ አፍሪካ ግጭትን ከመረጠች ሩዋንዳም ጉዳዩን በተመሳሳይ መንገድ ታስተናግዳለች" ብለዋል።

የቃላት ልውውጡ በሁለቱ አገራት መካከል ላለፉት በርካታ ዓመታት ተዳክሞ የቆየውን ግንኙነት የበለጠ መሻከሩን አሳይቷል።

የደቡባዊ አፍሪካ መሪዎች ዛሬ የመሪዎች ጉባኤ የሚያካሂዱ ሲሆን የቀጣናው ኃይል "የሠላም አስከባሪ ሃይል አይደለም፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ቦታ የለውም" ሲሉ ካጋሜ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ቲሺሴኬዲ በበኩላቸው "ከእኛ ጎን ሲዋጉ" ነበር ላሏቸው የሳድክ ወታደሮች እና የተባበሩት መንግስታት የሠላም አስከባሪዎች ክብራቸውን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ እና ቻይናን ጨምሮ በርካታ አገራት የሩዋንዳ ኃይሎች ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኤኤም 23 ጥቃትን ተከትሎ ለሩዋንዳ የሚያደርጉትን ዕርዳታ እንደሚያቋርጡ ከገለጹ ከለጋሽ አገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን ይገኙበታል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ረቡዕ እለት እንደተናገሩት ከሆነ ዓመታዊው 40 ሚሊዮን ዶላር የሁለትዮሽ እርዳታ አደጋ ውስጥ ወድቋል። ጀርመንም ከአገሪቱ ጋር የነበራትን የዕርዳታ ውይይት መሰረዟን አስታውቃለች።