በሶማሊያ ፑንትላንድ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናገሩ

ጉዳና ላይ ስደተኞች ሲያዙ

የፎቶው ባለመብት, abdi

የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ብንሆንም እንግልት ይደርስብናል ሲሉ የፑንትላንድ ባለሥልጣንት ግን የሚያዙት ሕገወጥ ስደተኞች ናቸው ይላሉ

የሶማሊያ ራስ ገዝ ግዛት በሆነችው ፑንትላንድ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ማንነት የለየ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ ሲናገሩ ለቢቢሲ የግዛቲቱ ባለሥልጣን ግን ክሱን አስተባብለዋል።

በተለይ በግዛቲቱ ዋና ከተማ ጋሮዌ እንዲሁም በወደብ ከተማዋ ቦሳሶ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለቢቢሲ እንደገለጹት የመኖሪያ እና የስደተኛ ሰነዶችን ያሟሉ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ በማንነታቸው ላይ የተመሠረተ ጥቃት እየደረሰብን ነው ይላሉ።

ገጠመን የሚሉትን ማሳደድ እና ማንገላታት ለማምለጥ ሲሉ በግዛቲቱ ውስጥ ከተደበቁበት ሥፍራ ሆነው የደረሰባቸውን ችግር ከገለጹልን መካከል አንዱ የሆኑት እና ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የቦሳሶ ከተማ ነዋሪ ከ10 ዓመት በፊት ወደ ፑንትላንድ እንደሄዱ እና እዚያም ቤተሰብ እንዳፈሩ ይናገራሉ።

ሆኖም የግዛቲቱ አስተዳደር የሽብር ስጋት አለብኝ በሚል ለእንግልት እንደዳረጋቸው ይገልጻሉ። በውጭ ዜጎች ላይ ለሚደርሰው እንግልት እንደ ምክንያት የሚያነሱት ከአይኤስ አሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት አላችሁ የሚል ክስ በማቅረብ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

"እዚህ ያሉና በዚህ የሚያልፉ የውጭ ዜጎች በሙሉ ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት አላቸው፣ ከነርሱ ጋር ሆነው ይወጉናል በሚል ምክንያት ነው ጥቃት የከፈቱብን" የሚሉት ኢትዮጵያዊው በዚህም ምክንያት አስተዳዳሪዎቹ በቅርቡ አዲስ ሕግ ማውጣታቸውን ገልጸዋል።

"ሕጉ ማንኛውም የውጭ ዜጋ ከፑንትላንድ እንዲወጣ የሚያዝ ነው። ይህ ሕግ ደግሞ ቀድሞውኑም ሕዝቡ ውስጥ የነበረውን ለመጤዎች ያለን ጥላቻ አባብሶታል። በተለይ ደግሞ ከአይኤስ ዳይሽ አሸባሪ ቡድን ጋር ሆኖ ሲዋጋ የነበረ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሞቶ ተገኝቷል የሚል አሉባልታ መነዛቱ ጥቃቱን አባብሶታል።"

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በፑንትላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የግዛቲቱ አስተዳደር ካወጣው ሕግ በተጨማሪ አሁን ለሚፈጸመው ጥቃት እና እንግልት መበርከት ሌለው ምክንያት "ከትንሽ እስከ ትልቅ ሥራ ዕድል ወሰዱብን የሚል ቅሬታ ነው" መሆኑን ይጠቀሳሉ።

በግዛቲቱ ዋና ከተማ ጋሮዌ ነዋሪ የሆነው እና ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ሌላ ኢትዮጵያዊ በተፈጸመበት ድብደባ ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ገብቶ ሕክምና ማግኘቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከባለፈው ሰኞ ጥር 19/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ሕገወጥ የተባሉ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የውጭ አገራት ዜጎችን ስታዲየም ውስጥ ያጎረው የፑንትላንድ አስተዳደር በሙዝ መጫኛ ከባድ ተሽከርካሪዎች ኢትዮጵያውያንን በማሳፈር ወደ አገራቸው ለመመለስ ሲያጓጉዝ እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ይህንን በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ነው የተባለውን እንግልት እና ጥቃት በተመለከተ ቢቢሲ ሶማሊኛ የፑንትላንድ ግዛት፣ በሪ የተባለውን ዞን አስተዳዳሪ አብዱልኢሳቅ አሊ ሻርዶን ጠይቆ ምላሽ አግኝቷል።

አስተዳዳሪው "ፑንትላንድ ከሌሎች አገራት በመጡ አሸባሪዎች ተወራለች" በማለት፤ ስደተኞችን በተመለከተ ያለውን ሁኔታ ለማስተካከል የግዛቲቱ አስተዳደር እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ፈቃድ ሳይኖራቸውን በሕገወጥ ሁኔታ ወደ ግዛቲቱ በመግባት በመኖር ላይ ያሉ የሌሎች አገራት ዜጎችን በመለየት እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

ይህ እርምጃም በግዛቲቱ አስተዳደር የተመዘገቡ እና ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ ያላቸውን ብቻ የማይመለከት ሲሆን፣ ሕገወጥ የሆኑትን በመያዝ ወደ መጡባቸው አገራቸው እንዲመለሱ እያደረጉ መሆናቸውን አብዱልኢሳቅ አሊ ተናግረዋል።

የግዛቲቱ ባለሥልጣናት እየወሰዱት ካለው እርምጃ ጋር ተያይዞ በፑንትላንድ ግዛት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ተለይተን ይደርስብናል ያሉትን እንግልት እና ጥቃት አልተፈጸመም በማለት አስተባብለዋል።