በጉራጌ ዞን ሰባት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሞቱበትን ምክንያት እየመረመረ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

ምሥራቅ ጉራጌ ዞን

የፎቶው ባለመብት, sm

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በምሥራቅ ጉራጌ ዞን፣ መስቃን ወረዳ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን ለቢቢሲ አስታወቀ።

ኅዳር 6/2018 ዓ. ም. ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማ አቶ ኃይሌ አበራ የተባሉ ግለሰብ፣ ከባለቤታቸው እና ከስድስት ልጆቻቸው ጋር እራት ከበሉ በኋላ መታመማቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ የመገናኛ ብዙኃን ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ በመስቃን ወረዳ 10 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ እንደተያዙም አስታውቀዋል።

"ከወረዳው አስተዳደር እና ከወረዳው ዐቃቤ ሕግ ጋር በመተባበር የምርመራ ቡድን ተዋቅሯል" ሲሉ ኮማንደር ታጁ ተናግረዋል።

ኅዳር 6 ምሽት ላይ እራት ከተመገቡ በኋላ መታመማቸውን ተከትሎ የተወሰኑት የቤተሰቡ አባላት ወደ ቡታጅራ ሆስፒታል ሲወሰዱ የተቀሩት ወደ አዲስ አበባ ምኒሊክ ሆስፒታል ተወስደዋል።

"እራት እንደበሉ ወዲያውኑ በጠና ታመሙ። የአካባቢው ነዋሪዎች ተጋግዘው ወደ ሆስፒታል ወሰዷቸው" ሲሉ ኮማንደር ታጁ ገልጸዋል።

ሆኖም ግን ከስምትን የቤተሰቡ አባላት መካከል የሰባቱ ሕይወት አልፏል።

ሟቾቹ ልጆች ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት እስከ 17 ዓመት እንደሆነ እና በሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሞቱ ፖሊስ ገልጿል።

የህልፈታቸው ምክንያት "መርዛማ ነገር መመገባቸው" እንደሆነ እንደሚጠረጠርም አክሏል።

የልጆቹ አባት የ46 ዓመቱ አቶ ኃይሌ አበራ ኅዳር 10 እንደሞቱ ተገልጿል።

"አባትየው እና ስድስት ልጆቻቸው ሞተዋል። እናታቸው በሕይወት ተርፋለች። በጽሑፍ መግባባት እንደምትችል አውቀናል" ሲሉ ኮማንደር ታጁ አስረድተዋል።

እናት ወ/ሮ ዳመነች ዳንበል በምኒሊክ ሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል ይገኛሉ።

እስካሁን ድረስ አስተማማኝ መረጃ ባይገኝም ለቤተሰብ አባላቱ ህልፈት ምክንያት የሆነው መመረዝ እንደሆነ ፖሊስ ጠቁሟል።

የልጆቹ እናት በሕይወት ከተረፉ በምን ምክንያት መመረዙ እንደተከሰተ ለማወቅ እንደሚረዳ ፖሊስ አስታውቋል።

"እናትየው በሕይወት ከተረፈች የተሻለ መረጃ እናገኛለን ብለን እናምናለን" ሲሉ ኮማንደር ታጁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ "ምኒሊክ ሆስፒታል የተደረገው ምርመራ ውጤት እየተጠበቀ ነው። ምንድን ነው የተመገቡት? በምን ምግብ ነው የተመረዙት? የሚለውን በተመለከተ ሆስፒታሉ የምርመራውን ውጤት ለፖሊስ ሲያጋራ የሚታወቅ ይሆናል" ሲሉም አክለዋል።

ፖሊስ የቤተሰብ አባላቱን ህልፈት "አሳዛኝ" ሲል ገልጾታል።