ቻይና ዩናይትድ ኪንግደምን የምትሰልልበት ውስብስብ የስለላ መረብ

ክሪስቶፈር ካሽ እና ክሪስቶፈር ቤሪ የተባሉ ብሪታኒያውያን ለቻይና በመሰለል ተጠርጥረው ከተያዙ በኋላ ክሳቸው ውድቅ መደረጉ አነጋጋሪ ሆኗል።
ሁለቱም ክሱን አስተባብለዋል። ዐቃቤ ሕግ እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ደግሞ እርስ በእርሱ የሚጣረስ መረጃ አውጥተዋል።
ባለሥልጣናት ቻይና ለዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የደኅንነት ስጋት ናት ብለው በይፋ ለማወጅ አልደፈሩም።
ቻይና እንዴት ነው ዩኬ ላይ የምትሰለልው? የሚለውን ዘመናት የተሻገ ጥያቄ እንደ አዲስ ያጫረ ክስተት ነው።
ከቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ ቻይናውያን ሰላዮች ዲፕሎማት መስለው ይሰልላሉ። መረጃ አቀባዮችም ይመለምላሉ።
የክሪስቶፈር ካሽ እና ክሪስቶፈር ቤሪን ጉዳይ ሲመረምር የነበረው የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ምስክርነትም ይሄንን ያረጋግጣል።
የቻይና ደኅንነት ተቋም ከፖሊሲ አውጪዎች፣ ከመንግሥት ባለሥልጣና እና ከሌሎችም ተቋማት መረጃ መሰብሰብ ይፈልጋል።
አገራት ስለሌሎች አገራት መረጃ ማግኘት ይሻሉ። በተለያየ ደረጃ መረጃዎችን ይሰበስባሉ እንዲሁም ስለላ ያከናውናሉ።
ቻይና ዩኬን እንደምትሰልለው ዩኬም ቻይናን ትሰልላለች።
የዩኬ የስለላ ተቋም ኤምአይ5 ኃላፊ ሰር ኬን ማክሊም እንደተናገሩት ቻይና ከስለላ ባሻገር የደኅንነት ስጋት ልትፈጥር ትችላለች።
ቻይና ጠንካራ ኢኮኖሚ ስላላት ከቻይና ጋር መተባበር እንደሚጠቅም ሳይታለም የተፈታ ነው።
ሌበር ፓርቲ ከቻይና ጋር የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር ይሞክራል። ከቻይና ጋር መተባበር የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያስከትል ይችላል? የሚለው ግን ዋነኛ ጥያቄ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የፖለቲካ ተጽዕኖ
በቻይና እና ከአገሪቱ ውጪም ያሉ ሰላዮች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን እንደሚሆን ይገመታል።
አንድ አገር ስለላ የሚያከናውንበት መንገድ ለየትኞቹ ጉዳዮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይጠቁማል።
ቻይና ዋነኛ ግቧ ኮምኒስት ፓርቲው በሥልጣን እንዲቆይ ማድረግ ነው። የሌሎች አገራት ፖለቲካ ውስጥ ጫና ማሳደር፣ ከቻይና የከዱ ሰዎችን መከታተል እና የምጣኔ ሃብት ዕድገትን ለማስቀጠል መረጃ ማሰባሰብ ተጠቃሽ ግቦች ናቸው።
የቻይና የፖለቲካ ተጽዕኖ እያደገ መምጣቱ ዩናይትድ ኪንግደምን ያሰጋታል።
ኤምአይ5 በአውሮፓውያኑ 2022 ክርስቲን ሊ የተባለች የቻይና ሰላይ የዩኬ ምክር ቤት ውስጥ ሰርጋ መግባት መቻሏን ገልጿል።
ክርስቲን ክሱን አስተባብላለች። ኤምአይ5 "ለፖለቲካ ዓላማ" ሲል መግለጫ እንዳወጣባት ገልጻም ተቋሙን ከስሳለች። ክሱ ብዙም ርቀት አልሄደም።
ቤይጂንግ የፖለቲካ ሕይወታቸውን እየጀመሩ ያሉ የዩኬ ዜጎችን በመመልመል ዘለግ ላለ ጊዜ መረጃ እንዲያቀብሉ ለማመቻቸት ትሞክራለች።
ይሄ የስለላ መንገድ መረጃ ለመመዝበር የሚደረግ ሳይሆን፤ የፖለቲካ ተጽዕኖ ለመፍጠር ያለመ ነው።
ቻይናን የሚደግፍ አቋም ያላቸው ፖለቲከኞች ቁጥር እንዲጨምር የማድረግ አንድ ስልት ነው።
የቻይናን መንግሥት ተቃውመው በሌላ አገር ጥገኝነት የጠየቁ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ስለላም ይካሄዳል።
ለቲቤት ነጻነት የሚታገሉ የመብት ተሟጋቾች እና የሆንግ ኮንግ የዴሞክራሲ አክቲቪስቶች ላይ ቻይና ታነጣጥራለች።
ኤምአይ5 እንደሚለው ከሆንግ ኮንግ ሸሽተው ዩኬ ጥገኝነት የጠየቁ የመብት ተሟጋቾች ቻይና ባስተላለፈችው ትዕዛዝ ምክንያት ትንኮሳ ይደርስባቸዋል። እነዚህን ሰዎች ቻይና በመሰለልም ትታወቃለች።
ቻይና የሚቀርቡባትን የስለላ ክሶች ታጣጥላለች።
"ቻይና በሌሎች አገራት የውጭ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም፤ የምንሠራው በግልጽ ነው" ሲል በለንደን ያለው የቻይና ኤምባሲ መግለጫ አውጥቷል።
'የቻይና የስለላ ጉዳይ' በሚል በዩኬ የሚሠራጨው መረጃ ሐሰተኛ ነው ስትል ቻይና አቋሟን ገልጻለች።
"የቻይና ዕድገት ለሌሎች አገራት በር የሚከፍት እንጂ ስጋት የሚሆን አይደለም። በመሠረተ ቢስ ክስ 'ቻይና እየሰለለች ነው' ወይም 'ቻይና ስጋት ደቅናለች' በሚል የቻይናን ስም ለማጥፋት የሚደረግ ሙከራን እናወግዛለን" ሲል በለንደን ያለው የቻይና ኤምባሲ ክሶችን አስተባብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ውስብስቡ የስለላ መረብ
ቻይና ከበይነ መረብ ስለላ እና የመረጃ ምዝበራ ጋር በተያያዘም ስሟ ይነሳል።
አምና የሕዝብ እንደራሴዎችን ኢሜይል ሰርስሮ ለመግባት ሞክራለች የሚል ክስ ቀርቦባታል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ "ቻይና ለደኅንነታችን ስጋት ናት" ብለው ነበር።
ቻይና 'ሳልት ታይፉን' የተባለ ውስብስብ የቴሌኮምንኬሽን ስለላ ታከናውናለች ስትል ዩኬ ባለፈው ነሐሴ ከሳለች።
የዩኬ ብሔራዊ ደኅንነት ተቋም "የተመዘበረው መረጃ የቻይና የስለላ ተቋም የቴሌኮምንኬሽን መስመሮች እና ዓለም አቀፍ ዝውውሮች ላይ እንዲያነጣጥር ይረዳል" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
በአውሮፓውያኑ 2024 ምርጫ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ስልኮቻቸው የምዝበራ ዒላማ ሆነው እንደነበር ይፋ ተደርጓል።
ቻይና በለንደን በሚገኘው ሮያል ሚንት ሕንጻ አዲስ ኤምባሲ ልታቋቁም መሆኑ የስለላ ስጋቱን አባብሷል።
ከሕንጻው በታች የስለላ መስመሮች ሊዘረጉ እንደሚችሉ የሚያምኑ ቢኖሩም ስጋቱን የሚያጣጥሉ ባለሙያዎችም ጥቂት አይደሉም።
ቻይና ከርቀትም ቢሆን የመረጃ ምዝበራ ልትፈጽም ትችላለች የሚል ስጋት አለ።
የቀድሞው የአሜሪካ መንግሥት ተቀጣሪ ኤድዋርድ ስኖውደን የአሜሪካ፣ የዩኬ እና የቻይና የስለላ መረብ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ መረጃ አሾልኳል።
ቻይና በዋናነት ሰፊ የመረጃ ክምችት ማደን ላይ ታተኩራለች። የፋይናንስ፣ የግል፣ የጤና እና ሌሎችም መረጃዎች ታስሳለች።
የቀድሞ የዩኬ ብሔራዊ የበይነ መረብ ደኅንነት ኃላፊ ቻይና "የዩኬ ዜጎች ላይ" መረጃ ትሰበስባለች ብለዋል።
ይሄን መረጃ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ለማሠልጠን፣ በግለሰብና በአገር ደረጃ ያለውን ክፍተት ለማጥናት ወይም የዩኬ ዜጎችን አቋም የበለጠ ለመገንዘብ እንደምትጠቀምበት ይታመናል።

ስለላ እስከ ምን ድረስ?
ቻይና መረጃ በመመዝበር ከምትሰበስበው በተጨማሪ በምዕራባውያን አገራት ቅርንጫፍ ባላቸው የቻይና ተቋማት በኩልም እንደምትሰልል ይታመናል።
እያደገ የመጣውን የቻይና ምጣኔ ሃብታዊ አቅም እንዴት አገሪቱ ከምትደቅነው አደጋ ጋር ማመጣን ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ያለው አይመስልም።
ቻይናውያን የኑሮ ሁኔታቸው እስከተሻሻለ ድረስ የአንድ ፓርቲ አገዛዝን ተቋቁመው ሊቀጥሉ ይችላሉ።
ቻይና ከምዕራባውያን አገራት በተለየ ሁኔታ የምጣኔ ሃብት፣ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ፍላጎቷን ለማሳካት የተለያዩ መንገዶች ትከተላለች።
አዳዲስ ምርቶች ይፋ ሲደረጉ ወይም የንግድ ድርድሮች ሲካሄዱ ቻይና መረጃ ለማግኘት መሞከሯን ትቀጥላለች።
የአገር ምሥጢር ያልሆኑ በዩኒቨርስቲዎች የሚደረጉ የቴክኖሎጂ ምርምር ውጤቶችም ዒላማ ይደረጋሉ። እነዚህ የጥናት ውጤቶች ወታደራዊ እና ሲቪል ጥቅም ሊኖራቸው ይችላል።
ኤምአይ5 እንደሚለው ቻይና ተመራማሪዎችን በማጥመድ አዳዲስ የጥናት ግኝቶችን ለማወቅ ትሞክራለች።
የቀድሞው የአሜሪካ የስለላ ተቋም ባለሥልጣን አንድሪው ባገር "ዲጂታል መረጃ የወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ውቅር መሠረት ነው። እነዚህ መረጃዎች ሾልከው ሲወጡ ተቋማት ይሽመደመዳሉ" ይላሉ።
አገራት ምጣኔ ሃብታዊ የበላይነታቸውን ለማስቀጠል ምሥጢራቸውንም መጠበቅ እንዳለባቸው ይናገራሉ።
ቻይና በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያደረገች ከመምጣቷ አንጻር ምዕራባውያን አገራት የቻይናን ምርቶች መጠቀም ግዴታ ይሆንባቸዋል።
በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እና በሌሎችም ዘርፎች ቻይና ዋነኛ ተፎካካሪ ናት።
የቻይናው ሁዋዌ ግዙፍ የ5ጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ እያስፋፋ ነው። የምዕራባውያን ጥያቄ ደግሞ ምን ያህል እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ማመን እንችላለን? የሚለው ነው።
የቻይና ምርቶች በዋጋ ርካሽ ቢሆኑም ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው? ሌላው ጥያቄ ነው።
ቻይና ሠራሽ ምርቶችን ብዙኃኑ ከመጠቀማቸው አንጻር፤ ምናልባት ቻይናን የሚያስቀይማት ነገር ሲከሰት እነዚህን ምርቶች ማቅረብ ልታቆም ትችላለች የሚል ስጋትም አለው።
ቻይና በዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ናት። በውጭ ንግድም ተጠቃሽ አገር ናት። ቻይናን ከዓለም አቀፍ ገበያ ማስወጣት የሚታሰብ አይደለም።
የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት እና የስለላ/የደኅንነት ስጋት ምን ያህል አብረው የሚሄዱ ወይም የሚቃረኑ ናቸው? ለሚለው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ መስጠትም ከባድ ነው።















