የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ መሥሪያ ቤት ሰላዮችን ለመቅጠር ስውር መንገድ አዘጋጀ

በለንደን የሚገኘው የኤምአይ6 መስሪያ ቤት ህንጻ

የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ መሥሪያ ቤት የሆነው ኤምአይ6 በተለይም ሩሲያውያንን ሰላዮችን ለመቅጠር ጥቅም ላይ የሚውል ራሱን የቻለ "ዳርክ ዌብ" ወይም ስውር የበይነ መረብ አድራሻን ሥራ ላይ አዋለ።

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንደገለጸው "ሳይለንት ኮሪየር" የተሰኘው ይህ ደኅንነቱ የተጠበቀ የመልዕክት መለዋወጫ ድረገጽ የስለላ ተቋሙን የምልመላ ሂደት ቀላል በማድረግ ብሔራዊ ደኅንነትን ለማጠናከር ያለመ ነው።

ይህንን መድረክ በመጠቀም ሩሲያውያንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ ለዩናይትድ ኪንግደም ጠቃሚ መረጃን ለማቀበል ሰላይ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ለመመልመል እንደታቀደም ተገልጿል።

ከኃላፊነታቸው በመልቀቅ ሂደት ላይ የሉት የስለላ ድርጅቱ የኤምአይ6 ኃላፊ ሪቻርድ ሙር ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰላይ መሆን የሚችሉ ሰዎች በመሥሪያ ቤቱ የዩትዩብ ቻናል ላይ በተለቀቀ ቪድዮ ላይ የተቀመጠውን መመሪያ በመከተል ማንነታቸው ሳይታወቅ ዳርክ ዌቡን እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

የኤምአይ6 ኃላፊ አርብ ዕለት ባደረጉት የመጨረሻ ንግግር ከሩሲያ፣ ከቻይና፣ ከኢራን፣ ከሰሜን ኮሪያ እና ከሌሎችም ሀገራት የሚመጡ ሰላይ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች የሚቀጠሩበትን ድረገጽ ይፋ አድርገዋል።

ኃላፊው ከቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ባደረጉት በዚህ ንግግር፤ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ክፉኛ ተችተዋል። ፑቲን "ዩክሬንን ከመጠቅለል በመለስ" በድርድር ሰላምን የማምጣት ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ "ምንም ማስረጃ የለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ፑቲን በዩክሬን ላይ ሊሳካላቸው እንደማይችል የተናገሩት የስለላ ተቋሙ አለቃ ሪቻርድ "[ፑቲን] ማኘክ ከሚችለው በላይ ጎርሷል" ሲሉ ተችተዋል።

የሩስያ ኢኮኖሚ እና የሥነ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ውድቀት ውስጥ እንደገባች ጠቅሰው፤ "የፑቲን ጦርነትም ይህንን እያፋጠነ ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኤምአይ6 ኃላፊው ቻይና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲሁም ለሰላማዊ እና ለጦር የሚውሉ ሁለት ጥቅም ያላቸው ምርቶችን በማቅረብ ሩሲያን እንደገፈች ነው ሲሉም ክስሰዋል።

ቻይና "ለጦር መሳሪያዎቻቸው የሚውሉ ኬሚካሎችን እና በሚሳዔሎቻቸው ውስጥ የሚገጠሙ የኤሌክትሮኒክ ክፍሎችን" እያቀረበች ነው በማለት ወቅሰዋል።

የቻይና እንዲሁም የኢራን እና የሰሜን ኮሪያ ድጋፍ ፑቲን ትርጉም ያለው ስምምነት ውስጥ እንዳይገቡ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር አዲሱ ድረገጽ ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ አርብ ዕለት ባደረጉት ንግግር፤ "ብሔራዊ ደኅንነትን ማስጠበቅ የማንኛውም መንግሥት ቀዳሚ ግዴታ" መሆኑን ገልጸው ነበር።

"ዓለም እየተቀየረ እና የሚያጋጥሙን ስጋቶች እየበዙ ሲሄዱ፤ ዩናይትድ ኪንግደም ሁልጊዜ ከጠላቶቻችን አንድ እርምጃ ቀድማ እንደምትገኝ ማረጋገጥ አለብን" ብለዋል።

"አሁን ኤምአይ6 በሩሲያ እና በመላው ዓለም ለዩናይትድ ኪንግደም አዳዲስ ሰላዮችን መመልመል እንዲችል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እያጠናከርነው ነው" ሲሉም አክለዋል።

ከሽብርተኝነት ወይም ከጠላት የስለላ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ዩናይትድ ኪንግደምን ማነጋገር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከአርብ ጀምሮ የበይነ መረብ አድራሻውን (ፖርታል) መጠቀም እንደሚችል ተገልጿል።

ድረ ገጹን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያስረዳ መመሪያ በተቋሙ የዩትዩብ ገጽ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎችም ወደ ገጹ ሲገቡ ታማኝ ቪፒኤን እንዲጠቀሙ እንዲሁም የራሳቸውን መሳሪያ እንዳይጠቀሙ ተመክሯል።

ኤምአይ6 ይህንን ዘዴ ይፋ ያደረገው የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ በ2023 በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ቪድዮ በመልቀቅ ሩሲያውያን ሰላዮችን ለመልመል ያደረገውን ጥረት በመከተል ነው።

ቻይና ከዚህ ቀደም ሲአይኤ ሰላዮችን ለመመልመል የሚጠቀምበትን ዳርክ ዌብ ሰብራ መግባቷን ተከትሎ ብዙ ተቀጣሪዎቹን አጥቷል።

አንድ ባለሥልጣን ይህ ክስተት በቅርብ ዓመታት ከታዩ ተመሳሳይ የደኅንነት መረጃ ክሽፈቶች እጅጉን የከፋው እንደሆነ ተናግረዋል።