ከሩሲያ ወደ ጀርመን በተዘረጋው የተፈጥሮ ጋዝ መስመር ፍንዳታ የተጠረጠረ ዩክሬናዊ በቁጥጥር ስር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Danish Defence handout
በአውሮፓውያኑ 2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከፈጸመች ከጥቂት ወራት በኋላ፤ በባልቲክ ባሕር ስር የተዘረጋውን ኖርድ ስትሪም የተፈጥሮ ጋዝ መስመር በማፈንዳት የተጠረጠረ ዩክሬናዊ ጣሊያን ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን የጀርመን ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
እንደ ዐቃቤ ሕጉ ገለጻ፤ 'ሰርሂ ኬ' በሚል ስያሜ የተጠራው ግለሰብ የተያዘው በጣልያኗ ሪሚኒ ግዛት ውስጥ ነው።
ግለሰቡ፤ ከሩሲያ ወደ ጀርመን የተፈጥሮ ጋዝ በሚያስተላልፉት የኖርድ ስትሪም 1 እና ኖርድ ስትሪም 2 መስመሮች ስር ፈንጂዎችን የጣለ ቡድን አባል እንደነበረም ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ጦርነት ምክንያት የኃይል ቀውስ እያጋጠማቸው በነበረበት ወቅት የተፈጸሙት ፍንዳታዎች፤ ለአውሮፓ ቁልፍ የተፈጥሮ ጋዝ ምንጭ እንዲቋረጥ ምክንያት ሆነዋል።
እስካሁን ድረስ የትኛውም አካል ለተፈጸመው ጥቃቱን ኃላፊነት ያልወሰደ ሲሆን፣ ዩክሬንም በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ እንደሌላት ገልጻለች።
በጣሊያን ካራቢኔሪ ወታደራዊ ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለው ዩክሬናዊ ከጥቃቱ ዋነኛ አቀነባባሪዎች አንዱ እንደሆነ ተጠርጥሯል።
ግለሰቡ ከጀርመን ወደብ ሮስቶክ ጀልባ በመከራየት ከዴንማርክ ደሴት ቦርንሆልም አቅራቢያ ወደሚገኝ የባልቲክ ባሕር አካባቢ የተጓዘ ቡድን አባል እንደሆነ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ምንም እንኳ ኖርድ ስትሪም 2 ወደ ሥራ ባይገባም፤ ከሩሲያ የባሕር ዳርቻ እስከ ሰሜን ምሥራቅ ጀርመን ድረስ በባልቲክ ባሕር ሥር 1,200 ኪ.ሜ ርዝመት ላይ የተዘረጉት የኖርድ ስትሪም 1 ሁለት መስመሮች የተረጋጋ አቅርቦት ሲያደርሱ ነበር።
የሞስኮ ወረራ በዩክሬን ላይ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ጀርመን፤ ግዙፉ በሩሲያው የተፈጥሮ ጋዝ አቅራቢ ጋዝፕሮም 100 በመቶ በባለቤትነት የተያዘውን ኖርድ ስትሪም ሁለትን ለማፅደቅ የጀመረችውን ሂደት ሰርዛለች።
ከወራት በኋላ ሩሲያ ኖርድ ስትሪም አንድን ዘግታለች።
መስከረም 2022 ላይ ደግሞ ከአራቱ የቧንቧ መስመሮች መካከል ሦስቱን ያወደሙት በርካታ ፍንዳታዎች ተፈጽመዋል።
የጥቃት አድራሾቹን ማንነት ምሥጢራዊ ሆኖ ቆይቷል።
የምዕራቡ ዓለም ሩሲያን የጠረጠረ ሲሆን፣ ሞስኮ ደግሞ አሜሪካን እና ብሪታኒያን ተጠያቂ አድርጋለች።
ባለፈው ዓመት የወጡ የጀርመን ሪፖርቶች፤ ዩክሬናውያንን ካፒቴኖችን የያዘ ቡድን ጀልባ በመከራየት ጥቃቱን ለመፈጸም ወደ ባልቲክ መጓዙን አመልክተው ነበር።
የጀርመን ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ቮሎዲሚር ዚ የተባለ ካፒቴን በቁጥጥር ስር እንዲውል ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
ሪሚኒ ውስጥ የተያዘው ተጠርጣሪ ከጣልያን እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ሐሙስ ዕለት መርማሪ ዳኛ ፊት እንደሚቀርብ ተነግሯል።
ዐቃቤ ሕግ ግለሰቡ "በጋራ ፍንዳታ በመፈጸም እና ሕገ መንግሥቱን በማዳከም የማጥፋት ወንጀል ከፍተኛ ተጠርጣሪ ነው" ብሏል።
እስካሁን ድረስ ዩክሬንን፣ ሩሲያን ወይም ማንኛውንም ሌላ ሀገር ከጥቃቶቹ ጋር የሚያገናኝ ማስረጃ የለም።















