ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ

የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ በዋሺንግተን ዲሲ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ያስቆማል የተባለ የሰላም ስምምነት እና ሰፊ ቀጠናዊ የምጣኔ ኃብት ውህደት ማዕቀፍ ተፈራረሙ።

በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ "የኢኮኖሚ እና የሀብቶች ደህንነትን ለማስቀጠል እና የረጅም ጊዜ ልማትን ለሁለቱም አገራት ጥቅም ለማጎልበት የጋራ ፍላጎት እንዳላቸው" ቃል በመግባት ረጅም የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተገኙበት የተፈረመውን ይህን የሰላም ስምምነት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ እና የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ አድንቀዋል።

ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ "ለዓለም፣ ለአፍሪካ ታላቅ ቀን ነው፤ እነዚህ ሁለት አገራት ሊኮሩበት የሚገባ ብዙ ነገር አላቸው" ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ካጋሜ በበኩላቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕን "ለማንም የማያዳሉ" መሪ በማለት ሰላም ለማምጣት ያለውን ዕድል "ወዲያውኑ" የተጠቀሙ ናቸው ብለዋቸዋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል ስምምነት ተፈርሞ ነበር፥

ነገር ግን ስምምነቱ ወዲያውኑ የፈረሰ ሲሆን ለዚህም ሁለቱ አገራት አንዳቸው ሌላኛቸውን ከስሰዋል።

ከስምምነቱ በፊት በማዕድን ሀብት በበለፀገው የምሥራቅ ኮንጎ በመንግሥት እና በሩዋንዳ ይደገፋል በሚባለው አማፂ መካከል የሚካሄደው ውጊያ ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ አገራቸው ከሁለቱም አገራት ጋር ወሳኝ የሆኑ ማዕድናትን ለመጠቀም የሚያስችል "አዳዲስ የዕድል በሮችን የሚከፍት" የተባለ ስምምነት መፈራረሟን ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነቱ ለአስርት ዓመታት በቀጠናው ሲካሄድ የቆየው ጦርነት እንዲቆም እና ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረስ፣ አማፂያን ትጥቃቸውን እንዲፈቱ፣ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እንዲመለሱ እንዲሁም አዲስ የኢኮኖሚ ብልጽግና ማዕቀፍን የያዘ መሆኑን ትራምፕ በሰላም ሰምምነቱ ወቅት ተናግረዋል።

ትራምፕ "በሁለቱ መሪዎች ላይ ጠንካራ እምነት አለኝ" ያሉ ሲሆን "ይህንን የገባነውን ቃል እንጠብቃለን" ብለዋል።

ካጋሜ እና ቲሺሴኬዲ ስምምነቱን እንደሚያከብሩ ተናግረው፣ ካጋሜ ትራምፕን ለሰላም አስተዋጽኦ ለማድረግ ያለውን ዕድል የሚጠቀሙ "መርህ ያላቸው" እና "የማያዳሉ መሪ" ሲሉ አንቆለጳጵሰዋቸዋል።

ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች ይህ የሰላም ስምምነት ለዓመታት የዘለቀውን ጦርነት በማስቆም ረገድ በጎ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

ነገር ግን አሁን እየተደረጉ ያሉ ውጊያዎች ግን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ረዥም ርቀት እንደሚቀር ያሳያሉ ሲሉ አክለዋል።

ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የኤም 23 አማፂያን በኳታር በተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል።

የመርሆዎች መግለጫ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ስምምነት ሁለቱም ወገኖች ከጥቃት፣ "የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ" እና "በመሬት ላይ ያሉ አዳዲስ ቦታዎችን በኃይል ለመያዝ ከሚደረጉ ሙከራዎች" መቆጠብ አለባቸው ይላል።

በሰላም ስምምነቱ ላይ እንዲታደሙ የተጋበዙ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ነበሩ።

የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር እና የአንጎላ ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሎሬንሶ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ከተገኙ መሪዎች መካከል ይገኙበታል።

ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሎሬንሶ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ያሸማገሉ ሲሆን በሁለቱ "ወንድማማቸች" አገራት መካከል ለ30 ዓመታት የዘለቀውን ግጭት የሚያስቆም ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የግሬት ሌክስ አገራት በርካታ ሀብት እና እምቅ አቅም ያላቸው አገራት ናቸው ሲሉ ተስፋቸውን ገልፀዋል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው የተፈረመውን ቀጠናዊ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ በማድነቅ የሰላም ስምምነቱ አፍሪካ ላላትን ሰፊ ሀብት በር የሚከፍት ነው ብለዋል።

ትራምፕ በሰላም ንግግሩ "ታሪካዊ" ስኬት አስመዝግበዋል ሲሉ ያደነቁት ሩቶ "ድፍረት የተሞላበት አመራራቸውን ተግባራዊ አድርገዋል" ብለዋል።