ቲክቶክ ገዢ ካላገኘ ወይም ስምምነት ላይ ካልተደረሰ በአሜሪካ ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ ይዘጋል

በቻይናውያን ባለሀብቶች ባለቤትነት የተያዘው ቲክቶክ በአሜሪካ ገዢ እየፈለገ ባለበት በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ እና የቻይና ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት በስፔን የንግድ ድርድር ማድረግ ጀመሩ።

ድርድሩ የሚመራው በአሜሪካው የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት እና የቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሂ ላይፌንግ ሲሆኑ፣ በሁለቱ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባላቸው አገራት መካከል የንግድ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ።

የዋሽንግተን እና የቤይጂንግ ከፍተኛ ልዑካን ለመጨረሻ ጊዜ ተገናኝተው የተወያዩት በሐምሌ ወር ሲሆን፣ የቀረጥ ስምምነቱን እስከ ኅዳር 10/2025 ድረስ ለ90 ቀናት አራዝመዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ቲክቶክ እንዲታገድ ሲወተውቱ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ይህንን አቋማቸውን በመቀየር ለሦስት ጊዜ ያህል መተግበሪያው የሚታገድበትን ጊዜ አራዝመዋል።

ትራምፕ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች እንዳሉት "እንዲሞት ልንተወው [ቲክቶክን] እንችላለን። ወይንም ደግሞ... አላውቅም። ሁኔታዎች አሁን በቻይና ላይ የተመሠረተ ነው። ብዙም ግድ የሚሰጥ ጉዳይ አይደለም" ብለዋል።

ቲክቶክ በአሜሪካ የሚታገድበት የመጨረሻው ቀን ረብዕ ሲሆን፣ ለአራተኛ ጊዜ ሊራዘም ይችላል የሚል ተስፋ አለ።

ባለፈው ወር ፕሬዝዳንት ትራምፕ ገዢ እስኪገኝ ድረስ የሚዘጋበትን ቀን ሊያራዝሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ከመተግበሪያው ጋር ተያይዞ የሚነሳው የብሔራዊ ደኅንነት እና የግላዊ መረጃ ምንተፋ ስጋትን "የተጋነነ" ብለውታል።

ቢቢሲ ከቲክቶክ ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንቱ የሰጡትን አስተያየት በሚመለከት ዋይት ሐውስን አስተያየት ቢጠይቀም ምላሽ አላገኘም።

መተግበሪያው በመላው ዓለም ቢሊዮኖች የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ በአሜሪካ ብቻ 170 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት።

በዚህ ሳምንት ልዑካን ቡድኑ ከተወያየ በኋላ ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በጥቅምት ወር ተገናኝተው ስለሚወያዩባቸው ጉዳዮች ያነጋገራል ተብሎ ይጠበቃል።

በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የተደረሰው የታሪፍ ስምምነት ሁለቱ አገራት በሚልኳቸው ምርቶች ላይ ጥለውት የነበረውን ከፍተኛ ታክስ መቀነስ የቻለ ነበር።

የቀኑ መራዘም ሁለቱ አገራት "ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ተግባራት" ባሉት ላይ ለመደራደር ዕድል የሚሰጣቸው ሲሆን፣ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮችም ተነስተው ውይይት እንደሚደረግባቸው ዋይት ሐውስ አስታውቋል።