ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቲክቶክ ‘ማኅበራዊ መስተጋብርን ያደፈርሳል’ በሚል በኔፓል ታገደ
ኔፓል በቲክቶክ የሚተላለፉ ይዘቶች ‘ማኅበራዊ መስተጋብርን ያደፈርሳሉ’ በሚል ምክንያት ግዙፉን የቻይና መተግበሪያ አገደች።
ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ወርሃዊ ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክቶክ በሕንድ እና ፓኪስታን ጨምሮ በተለያዩ አገራት እግድ ተላልፎበታል። ሞንታና መተግበሪያውን በማገድ የአሜሪካ የመጀመሪያዋ ግዛት መሆኗ ይታወሳል።
ቲክቶክ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ይሰጣል ከተባለ በኋላ በበርካታ መንግሥታት በአይነ ቁራኛ ይታያል።
የኔፓል የኮሚኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትር ሬክሃ ሻርማ በቲክቶክ የሚተላለፉ ይዘቶች አሉታዊ ተጽእኖ ያላቸው ናቸው ብለዋል።
ሚንስትሯ ጨምረውም የእግድ ትዕዛዙ በአስቸኳይ የሚፈጸም መሆኑን እና የቴሌኮም አስተዳዳሪዎች ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንደተነገራቸው ጨምረው ተናግረዋል።
የኔፓል መንግሥት መተግበሪያውን የሚያግደው ይዘቶቹ ጎጂ ናቸው በሚል ምክንያት ይሁን እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ውሳኔው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፍ ነው ብለዋል።
ጋጋን ታፓ የተባሉ የምክር ቤት አባል መንግሥት በቲክቶክ የሚተላለፉ ይዘቶችን ሳንሱር ማድረግ አለበት እንጂ መተግበሪያውን ጨርሶ መዝጋቱ የመብት ጥሰት ነው ብለዋል።
ቲክቶክ ከተጠቃሚዎች ቁጥር አንጻር ከፌስቡክ እና ኢንስታግራም ጋር ባይነጻጸርም ወጣት የሆኑ ተጠቃሚዎቹ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረለት ነው።
በኔፓል ብዙ ተጠቃሚዎች ካሏቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎች መካከል ቲክቶክ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።