ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቱርክ ለገና እና አዲስ ዓመት የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ ነበር የተባሉ 115 የአይኤስ አባላት ተያዙ
በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ገና እና አዲስ ዓመት በሚከበሩባቸው ቀናት ሊፈጸሙ ታቅደው የነበሩ የሽብር ጥቃቶችን ማክሸፉን የቱርክ መንግሥት አስታወቀ።
ከታቀዱት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) አባላት ናቸው የተባሉ ከ100 በላይ የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በቱርክ መዲና ኢስታንቡል በ124 ቦታዎች ፍተሻ መካሄዱን ዋና ዐቃቤ ሕግ ተናግረዋል። በፍተሻው የጦር መሣሪያ፣ ጥይት እንዲሁም 'ተቋማዊ ሰነዶች' መያዛቸውን ገልጸዋል።
የቱርክ ባለሥልጣኖች እንዳሉት የአይኤስ ደጋፊዎች በዋናነት ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን ዒላማ በማድረግ በቱርክ ውስጥ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲያቅዱ ነበር።
እስካሁን 115 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ተጨማሪ 22 ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ አሰሳ እየተካሄደ ይገኛል።
የዐቃቤ ሕግ ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት ተጠርጣሪዎቹ ከቱርክ ውጭ ከሚገኙ የአይኤስ አባላት ጋር ግንኙነት ነበራቸው።
የቱርክ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ተጠርጣሪዎቹ ከመያዛቸው ከሁለት ቀናት አስቀድሞ በአፍጋኒስታን እና ፓኪስታን ድንበር ላይ ፍተሻ አድርጓል።
በአይኤስ ውስጥ ከፍተኛ አመራር የሆነ ቱርካዊ ዜጋ ንጹኃን ላይ ጥቃት ለማድረስ በማሴር በቁጥጥር ሥር ውሏል።
የቱርክ የፀጥታ ባልደረቦች ከአይኤስ ጋር ትስስር አላቸው የሚባሉ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ እርምጃ ይወስዳሉ።
አይኤስ በሶሪያ ውስጥ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል። ቱርክ ከሶሪያ ጋር 900 ኪሎሜትር የሚረዝም ድንበር ትጋራለች።
የሶሪያ ፕሬዝዳንት አሕመድ አል-ሻራ ከቱርክ መንግሥት ጋር በቅርበት ይሠራሉ። ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አገራት ጋር በመጣመር አይኤስ ላይ በጥምረት እርምጃ ለመውሰድ ተስማምተዋል።
ያለፈው ሳምንት አሜሪካ በሶሪያ ተከታታይ የአየር ጥቃቶች መፈጸሟ ይታወሳል። ሦስት አሜሪካውያን መገደላቸውን ተከትሎ የተወሰደ የአጸፋ እርምጃ ነው።
በዚህ ወር መባቻ ላይ አሜሪካውያን የሆኑ ሁለት ወታደሮች እና አንድ አስተርጓሚ በአይኤስ ተገድለዋል።