ስለ አዋሽ ፈንታሌ የመሬት መንቀጥቀጥ የሰመራ ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች እና የወረዳው አስተዳዳሪ ምን አሉ?

እሁድ ምሽት እስከ አዲስ አበባ ድረስ ንዝረቱ የተሰማው የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተበት የአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ፤ ከ700 በላይ በከሰም ግድብ እና ፈንታሌ ተራራ አካባቢ የነበሩ ነዋሪዎችን አስቀድሞ ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወሩን አስታወቀ።

የትናንቱን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአካባቢው በተከሰቱ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጦች ትምህርት ቤት እና መስኪድን ጨምሮ በአራት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የወረዳው አስተዳደር ለቢቢሲ ገልጿል።

እሁድ መስከረም 26/2017 ዓ.ም. ምሽት ሁለት ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ በክልሉ ጋቢ ራሱ ዞን አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ንዝረቱ አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ከተሞች ድረስ የተሰማ ነበር።

በሬክተር ስኬል 4.9 ሆኖ የተመዘገበው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ 10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ያለው እንደነበር “ኧርዝ ክዌክ ትራክ” የተሰኘው የመሬት መንቀጥቀጥ መከታተያ ድረ ገፅ ዘግቧል።

የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባህ አባህ ሁሴን፤ የትናንቱ የመሬት ነውጥ “መጠኑ ሰፋ ያለ እና አስደንጋጭ” እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተበት ሰዓትም በወረዳው በሚገኘው ፈንታሌ ተራራ አካባቢ ላይ “ከፍተኛ ድምፅ እና ፍንዳታ” ተሰምቶ እንደነበር የወረዳ አስተዳዳሪው ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ [ሰኞ ረፋድ] ፍንዳታው ወደ ተከሰተበት አካባቢ ተጉዘው አለመመልከታቸውን አክለዋል።

“ተራራው መፈንዳት የጀመረው የመሬት መንቀጥቀጡ ሲያጋጥም ነው። ፍንዳታው ካጋጠመ በኋላ ትንሽ ሻል የማለት ሁኔታ ተከስቷል” ሲሉ በሰዓቱ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል። ዋና አስተዳዳሪው፤ ከመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ምሽት አምስት ሰዓት ከ16 ደቂቃ አካባቢ “መጠነኛ የመንቀጥቀጥ ሁኔታ” መከሰቱን አስረድተዋል።

በትናንቱ ክስተት በሰዎች እና በእንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የገለጹት አቶ አባህ፤ በወረዳው ሳቡሬ ቀበሌ የሚገኘው ሳቡሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ መሰንጠቅ መከሰቱን ገልጸዋል።

በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በቤቶች እና በመሬት ላይ መሰንጠቅ እንዲሁም መፍረስ ሲያጋጥም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከመስከረም 17 አንስቶ እስካሁን ድረስ አምስት የመሬት መንቀጥቀጦች አካባቢው ላይ መከሰታቸውን የ“ኧርዝ ክዌክ ትራክ” መረጃ ያሳያል። የመሬት መንቀጥቀጦቹ በሬክተር ስኬል ከ4.5 እስከ 4.9 ሆነው የተመዘገቡ እንደሆኑም ተዘግቧል።

አካባቢው ላይ በተከሰቱት ተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጦች በአንድ መስኪድ እና በሁለት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አባህ ገልጸዋል። በአካባቢው የሚገኘው መስኪድ “የፊት ሽፋኑ” እንደተገነጠለ እና መሰንጠቅ እንዳጋጠመው የሚናገሩት አቶ አባህ፤ ሁለቱ ቤቶች ደግሞ የጎን ክፍላቸው ላይ መፍረስ መከሰቱን አስረድተዋል።

ባለፉት ቀናት በወረዳው የታዩት እነዚህ ክስተቶች በሳቡሬ ቀበሌ የተለያዩ የመሬት ስንጥቆች ለመፈጠራቸው ምክንያት እንደሆኑ ሁለት የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ትምህርት ቤት መምህራን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲው የሚገኘው የሥነ ምድር ትምህርት ቤት ሦስት መምህራን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ ባለው የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ወረዳ የመስክ ምልከታ አድርገው እንደነበር የሥነ ምድር ትምህርት ቤት ዲን አቶ ጌታቸው ወልደጻድቃን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ወደ ቀበሌው የተጓዘው ቡድን አባል የነበሩት አቶ ጌታቸው እንደሚገልጹት በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት በአካባቢው መሬት ላይ የተከሰተው ስንጥቅ “በጣም ረጅም” ነው። የመሬት ስንጥቁ ክፍል እስከ “1.5 ሜትር” የሆነባቸው አካባቢዎች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ ስንጥቆቹ የተፈጠሩት የአካባቢው ነዋሪዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች እንደሆኑም አስረድተዋል።

ወደ ሳቡሬ ቀበሌ የተጓዘው የዩኒቨርስቲው ቡድን አባል የሆኑት ሌላኛው የትምህርት ክፍሉ መምህር አቶ ኖራ ያሚኖም በበኩላቸው አካባቢው ላይ የተከሰቱት የመሬት መሰንጠቆች “ከዚህ በፊት በቦታው ያልነበሩ” እንደሆኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ተጨማሪ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሁለቱ የሥነ ምድር ባለሙያዎች ገልጸዋል። ይሁንና አካባቢው የሚገኘው “በዋናው የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ” በመሆኑ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ የሚጠበቅ እንደሆነ አመልክተዋል።

ከአሁን በኋላ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት ስለመቻሉ መናገር እንደማይቻል ሥነ ምድር ባለሙያዎቹ ገልጸዋል። ነገር ግን የመሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ የመሬት መንሸራተት እንዲሁም የድንጋይ መንከባለል ሊኖር ስለሚችል ተራራ ስር እንዲሁም የመሬት መሰንጠቅ ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ገላጣ ወደሆነ አካባቢ መዘዋወር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የሥነ ምድር ባለሙያዎቹ ነዋሪዎች እንዲርቁ ምክረ ሃሳባቸውን ካቀረቡባቸው ቦታዎች መካከል በወረዳው የሚገኘው የከሰም ግድብ ይገኝበታል። 500 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ያለው የከሰም ግድብ የሚገኘው በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች ለሚገኘው ከሰም ስኳር ፋብሪካ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።

የሥነ ምድር ትምህርት ቤት ዲኑ አቶ ጌታቸው፤ “እኛ የምንመክረው የመሬት መንቀጥቀጡ እንደዚህ ዓይነት ቀጣይነት ካለው ምን እንደሚፈጠር ስለማይታወቅ [በግድቡ] የታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ አካባቢዎች ወደተሻለ ቦታ እንዲመጡ ነው” ሲሉ ከግድቡ ጋር ተያይዞ ያለውን ስጋት አንስተዋል።

ሌላኛው ባለሙያ አቶ ኖራም፤ “የሬክተር ስኬሉ ከሰባት እና ከዚያ በላይ የሚደርስ ከሆነ ጉዳቱም በዚያው ልክ ከፍ ሊል ይችላል። በተለም [በግድቡ] የታችኛው ተፋሰስ ላይ በሚገኙ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል” ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል።

የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባህም የባለሙያዎቹን ስጋት እንደሚጋሩት ለቢቢሲ ተናግረዋል። የከሰም ግድብ “42 ኪሎ ሜትር” ስፋት ያለው መሬት ላይ የተኛ መሆኑን የሚያነሱት አቶ አባህ፤ ግድቡ ላይ ጉዳት የሚደርስ ከሆነ የሚያስከትለው አደጋ ከአዋሽ ፈንታሌ ወረዳም የሚሻገር ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።

የወረዳው አስተደዳር የመሬት መንቀጥቀጡን በተመለከተ ያለውን ስጋት ለክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ተቋም ማሳወቁን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል። በአካባቢው እያጋጠመ ያለውን ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎም ከሁለት ሳምንት በፊት በግድብ እና ተራራ ስር በሚገኙ አራት ሳይቶች ላይ ሰፍረው የነበሩ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወሩ መደረጉን አስታውቀዋል።

“አዋሽ ፈንታሌ የከሰም ግድብ ያለበት እንደመሆኑ ‘አስጊ ናቸው’ ካልናቸው ከአራት ሳይቶች ወደ 710 የሚሆኑ ሰዎች ከእነዚህ ቦታዎች ተነስተው ሌላ ቦታዎች ላይ እንዲሰፍሩ አድርገናል። ይህንንም ከፌደራል እስከ ክልል ላሉ አካላት አሳውቀናል” ሲሉ ወረዳው አስተዳደር የወሰደውን የጥንቃቄ እርምጃ ገልጸዋል።

በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ የተከሰተው ርዕደ መሬት በአካባቢው በቤቶች እና በመሬት ላይ መሰንጠቅን ያስከተለ ሲሆን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ ንዝረቱ በተሰማባቸው ቦታዎች የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።