በደቡብ አፍሪካ አባቶች ከእናቶች እኩል የወሊድ ፈቃድ እንዲያገኙ ተወሰነ

በወላጅ እና ህፃን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሁን ላይ ያለው ሕግ ለእናቶች አራት ወር ለአባቶች የ10 ቀን የወሊድ እረፍት የሚሰጥ ነው

የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ሁሉም ወላጆች እኩል የወሊድ እረፍት እንዲኖራቸው ወሰኗል።

ውሳኔው ትልቅ ውሳኔ እና ለፆታ እኩልነት እና የቤተሰብ መብት ግዙፍ አሸናፊነት ተደርጎ ተወስዷል።

በቀደመው ሕግ እናቶች የአራት ወር የወሊድ ፈቃድ ያላቸው ሲሆን አባቶች ደግሞ 10 ቀናት ብቻ ይሰጣቸው ነበር።

የአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ሕጉን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ያለው ሲሆን፤ ለአባቶች አድሎአዊ ነው ብሏል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ወላጆች እንደፈቀዱ የሚጠቀሙበት እኩል የወሊድ እረፍት እንዲያገኙ በይኗል።

'ሲንግል ዳድስ ኔትወርክ' የተባለ ድርጅት መስራች የሆኑት ሴትምቢሶ ፓኪቲ "ይህ ለእኩልነት፣ ለቤተሰብ ደኅንነት እና ለደቡብ አፍሪካ የወደፊት አባቶች ፈር ቀዳጅ እርምጃ ነው" ብለዋል።

እ.አ.አ በ2023 የአገሪቱ የታችኛው ፍርድ ቤት የአገሪቱ ሁለት ሕጎች የተወሰኑ ክፍሎች ፍትኃዊነት የጎደላቸው መሆናቸውን እንዳገኘ እና የበርካታ የቤተሰብ መብቶችን የሚጥሱ ናቸው ብሏል።

የጓተንግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሊድ ፈቃድ እና የሥራ አጥ ጥቅማ ጥቅሞችን ማግኘትን በተመለከተ ለወላጆችን ፍትኃዊ አለመሆኑን ወስኗል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጉዳዩ በብቸኝነት በሴቶች ላይ የሚጣለውን ማኅበረሰባዊ ጫና ፍትኃዊ ለማድረግ በወጠኑ በሁለት ጥንዶች፣ በፆታ እኩልነት ኮሚሽን እና በሌሎችም ወደ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን፤ የወላጅነት ኃላፊነት የጋራ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ተፈፃሚ እየሆነ ያለው ሕግ ለወላጅ እናት አራት ወራት የወሊድ እረፍት ሲሰጥ ለአባቶች፣ የጉዲፈቻ (አሳዳጊ) አባቶች፣ በማሕፀን ኪራይ አባት የሚሆኑ ዜጎች የ10 ቀናት የወሊድ እረፍት ብቻ መስጠት አድሏዊ ነው ሲል አቤቱታው አመልክቷል።

ብይኑን የሰጡት የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ዙኪሳ ሻቂ ይህን ሕግ ጊዜውን ያልዋጀ እና "ለእናቶች የብቸኝነት ሸክም እና አባቶችን ያገለለ" ነው ካሉ በኋላ ሁለቱም ወላጆች የተፈቀደላቸውን እረፍት በፈለጉት መልኩ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

"አባቶች የተገለሉ እና በጨቅላ ልጆቻቸው የመጀመሪያ ጊዜ ሕይወት ላይ እንዳይሳተፉ የነፈገ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ዳኛዋ ብይኑ የፆታ እኩልነት ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ ክብርን መጠበቅ መሆኑን ገልፀው፤ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የመጨረሻ ትኩረቱ የልጆች አስተዳደግ ነው ብለዋል።

"ፍትኃዊ ያልሆነው ሁኔታ ወላጆችን ያገለለ ብቻ ሳይሆን ልጆች እንክብካቤ በሚያስፍጋቸው እና አዲሱን ከበባቢያቸውን በሚላመዱበት በዚህ ወሳኝ ሕይወታቸው ከወላጆቻቸው ጋር እንዳይሆኑ የነፈገ ነው"።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ ፍርዱን በደስታ ቢቀበሉም የሕግ ባለሙያዎች ግን ውሳኔው በአሰሪዎች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ያስጠበቀቁ ሲሆን፤ አሰሪዎች ውሳኔውን ለመተግበር የእረፍት ፖሊሲዎቻቸውን ማስተካከል አለባቸው ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ከብይኑ ጋር በሚጣጣም መልኩ የእንደራሴዎች ምክር ቤት ሕጉን እስኪያሻሽል ድረስ የሦስት ዓመት ጊዜ ሰጥቷል።

ሕጉ እስኪሻሻል ድረስ ወላጆች የአራት ወራት እና የ10 ቀን የወሊድ እረፍታቸውን በምን መልኩ መጠቀም እንደሚፈልጉ መወሰን ይችላሉ ብሏል።