በሕንድ ቅንጡ ሆቴል ለሁለት ዓመት ሳይከፍል የቆየው የ70 ሺህ ዶላር ባለዕዳ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ ግለሰብ በሕንድ ዋና ከተማ ዴልሂ ውስጥ ካሉ ባለ አምስት ኮከብ ቅንጡ ሆቴሎች በአንዱ አምስት ሳንቲም ሳይከፍል ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ መክረሙ ተደረሰበት።
ግለሰቡ ውድ በሚባለው እና ከዴልሂ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ከሚገኘው ሮዜት ሐውስ ተብሎ ከሚታወቀው ሆቴል ውስጥ ለ603 ቀናት ክፍያ ሳይፈጽም በነጻ መቆየቱ ተነግሯል።
ግለሰቡ በሆቴሉ ውስጥ እየተስተናገደ ለቆየባቸው ጊዜያት 70 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መክፈል ይጠበቅበት ነበር። አሁን ግን የሆቴሉ ኃላፊዎች ለፖሊስ ጠቁመው በግለሰቡ ላይ ክስ ከፍተዋል።
የባለአምስት ኮከቡ ሆቴል ኃላፊዎች ግለሰቡ በሆቴሉ ውስጥ ከሚገኝ ሠራተኛ ጋር በመመሳጠር የሚጠበቅበትን ገንዘብ ሳይከፍል እንዲቆይ ለማድረግ ሳይችል አይቀርም ብለዋል።
ነገር ግን ከዚህ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው የለም።
ግለሰቡ የፈጸመው ማጭበርበር የተደረሰበት ከአንድ ወር በፊት ሲሆን፣ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ የተደረገው ግን ባለፉት ቀናት ነው።
ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብ ክፍል ይዞ ወደ ቅንጡው ሆቴል የገባው ለአንድ ቀን አዳር የነበረ ሲሆን፣ ባልታወቀ ሁኔታ ምንም ሳይከፍል ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ሲስተናገድ መቆየቱን ‘ኢንዲያን ኤክስፕረስ’ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
ምንም እንኳን ግለሰቡ በቆይታው ወቅት ክፍያ ባይፈጽምም፣ ያልታወቀ የሆቴሉ አንድ ሠራተኛ ቆይታውን እያራዘመለት ከ600 ቀናት በላይ በነጻ ሲዝናና ቆይቷል።
ግለሰቡ ይህንን ያህል ጊዜ እንዲቆይ መረጃው ከሌሎች እንግዶች ጋር እንዲደባለቅ ተደርጓል ወይም ከሌሎች ጋር እንዲቀያየር ተደርጎ ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል።
ሳይከፍል ሰባ ሺህ ዶላር የሚገመት አገልግሎትን ከሆቴሉ ያገኘው ግለሰብ ጉዳይ መነጋገሪያ ከመሆኑ ባሻገር ከቅንጡው የዴልሂ ሆቴል የአሰራር ደንብ ውጪም ነው ተብሏል።
በሆቴሉ አሰራር መሠረት ከ500 ዶላር በላይ ዕዳ ያለበት እንግዳ ጉዳይን የሆቴሉ ሥራ አስኪያጆች እንዲየውቁት ተደርጎ ሌላ አገልግሎት ከማግኘቱ በፊት እንዲከፍል መደረግ ይኖርበት ነበር።
ነገር ግን የግለሰቡን ጉዳይ በተመለከተ ምንም ነገር ሳይባል ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ያለክፍያ በሆቴሉ ውስጥ መቆየት እንደቻለ ፖሊስ ለጋዜጣው ገልጿል።












