በሴራሊዮን ታጣቂዎች ማረሚያ ቤት ሰብረው ገብተው እስረኞችን ማስለቀቃቸውን ተከትሎ የሰዓት እላፊ ታወጀ

ታጣቂ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሴራሊዮን ታጣቂዎች ማረሚያ ቤት ሰብረው ገብተው እስረኞችን ማስወጣታቸውን ተከትሎ አገር አቀፍ የሰዓት እላፊ ታወጀ።

በመዲናዋ ፍሪታውን በሚገኘው የማዕከላዊ ፓዴማ እስር ቤት የነበሩ ታራሚዎች እሁድ ማለዳ ማምለጣቸውንም የተቋሙ ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ታጣቂዎቹ በከተማዋ በሚገኝ አንድ ትልቅ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።

ለአገሪቱ ፕሬዘዳንት መኖሪያ ቤት ቅርብ በሆነው የጦር ሰፈር ህንጻ የተኩስ ድምጽ መስማታቸውንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ጥቃቱንም ተከትሎ የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር አስቸኳይ የሰዓት ዕላፊ ያወጀ ሲሆን የአገሪቱ ነዋሪዎችም በቤታቸው እንዲወሰኑ ጠንከር ያለ ትዕዛዝ ተላልፏል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ በበኩላቸው በአገሪቱ መረጋጋት ሰፍኗል እንዲሁም ታጣቂዎቹንም ለመያዝ የማደን ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ይሁንና መቀመጫውን በፍሪታውን ያደረገው የቢቢሲው ዘጋቢ ኡማሩ ፎፋና በከተማዋ ስርዓት አልበኝነት እንደሰፈነ ዘግቧል።

‘ሴንትራል ፓዴማ ሮድ’ ከተሰኘው እስር ቤት ምን ያህል ታራሚዎች እንዳመለጡ በትክክል ባይገለጽም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጥቂት ዓመታት በፊት ባሰፈረው መረጃ መሰረት ከ2 ሺህ በላይ ታራሚዎችን መያዙን ያሳያል።

በማህበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ቪዲዮዎች እንዳሳዩት በርካታ ታራሚዎች ከእስር ቤት ሲሸሹ ያሳያል።

ከእነዚህም መካከል በዘረፋ ክስ ባለፈው ዓመት ለእስር የተዳረገው ታዋቂው ራፐር ቦስ ኤልኤጄ በነጻነት ሲሮጥ የሚያሳይ ቪዲዮም አንዱ ነው።

ቢቢሲ የእነዚህን ቪዲዮዎች ትክክለኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዴባ ለሁለተኛ ጊዜ አገሪቱን ለመምራት በሰኔ ወር የተደረገውን ምርጫ አሸንፌያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ በሴራሊዮን የፖለቲካ ውጥረት ነግሷል።

ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫው ወጥነት ያልነበረው እንዲሁም ቆጠራው ግልጽነት የጎደለው እና ኃይል እና ማስፈራራቶች የነገሰበት ነበር ሲሉ አውግዘውታል።

በነሐሴ ወር በርካታ ወታደሮች ፕሬዚዳንቱን በመፈንቅለ መንግሥት ለመጣል አሲረዋል በሚል በቁጥጥር ስር ውለው ተከሰዋል።

ጎረቤቷን ጊኒን ጨምሮ በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ የሚገኙ ስምንት አገራት መፈንቅለ መንግሥት ማካሄዳቸውን ተከትሎ በወታደራዊ አገዛዝ ስር ይገኛሉ።