የፌስቡክ ባለቤት ሜታ 13 በመቶ ሰራተኞቹን ሊቀንስ ነው

የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ 13 በመቶ የሚሆነውን የሰው ኃይል እንደሚቀንስ አስታወቀ።

በተቋሙ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቅነሳ የተባለ ሲሆን 11 ሺህ ሰራተኞች ከስራ ተሰናብተዋል።

ሜታ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ87 ሺህ በላይ ሰራተኞች አሉት።

የሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ ቅነሳው "በሜታ ታሪክ ውስጥ ካደረግናቸው በጣም አስቸጋሪ ለውጦች" ዋነኛው ነው ብሏል።

ይህ ዜና የተሰማው ትዊተር ግማሽ የሚሆኑ ሰራተኞቹን እንዲሁም ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን መቀነሳቸውን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ነው።

“ይህ ለሁሉም ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ እናም በተለይም በዚህ ለተጎዱት አዝናለሁ” ሲልም በመግለጫው አትቷል።

ማርክ ዙከርበርግ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ኩባንያው ባገኘው የገቢ ጭማሪ ላይ በመመርኮዝ ተቋሙ ከፍተኛ ዕድገት ይኖረዋል በሚል መጠበቁን ወቅሷል።

"በርካቶች በወረርሽኙ ወቅት የተከሰተው ዕድገት ዘላቂ እንደሚሆን ተንብየው ነበር" ሲል በመግለጫው ጠቁሟል

 "እኔም ይህንኑ ነበር የጠበቅኩት ስለዚህም ኢንቨስትመንታችንን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ወሰንኩ” ብሏል።

ይልቁንም “የማክሮ ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል” እና “ፉክክር መጨመር” ገቢው ከሚጠበቀው በላይ እንዲቀንስ አድርጓል ብሏል።

“የፈጸምነው ስህተት ገብቶኛል፤ እናም ለዚያ ሀላፊነቱን እወስዳለሁ" ብሏል።

የሰራተኞች ቅነሳ በሰፊው እየተጠበቀም ነበር።

ማርክ ዙከርበርግ ማክሰኞ ዕለት በመቶዎች ለሚቆጠሩ የሜታ ስራ አስፈጻሚዎች ሰራተኞቹን የመቀነስ እቅድ እንዳለው ማስታወቁን ሲል ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

ዙከርበርግ ኩባንያው ከፍተኛ ዕድገት በሚያስገኙና የረዥም ጊዜ ራዕይ በሚያረጋግጡ እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ማስታወቂያ እና ዘርፎች ላይ ያተኩራል።

ሜታ ሌሎች ወጪዎችንም እንደሚቀንስ አስታውቋል። ከነዚህም መካከል ህንፃዎች እና ቢሮዎች ላይ ያለውን ወጪ መቀነስ እና ቢሮ መጋራትንም እንደሚጨምር አስታውቋል።

የተቀነሱት የሜታ ሰራተኞች በቅርቡ ኢሜይል እንደሚደርሳቸው እና ጥያቄዎችን የመጠየቅ እድል እንደሚኖራቸው ተናግሯል።