እስራኤል የጋዛ ሰርጥ ወረራን ጀምራለች?

የፎቶው ባለመብት, EPA
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ እያደረገችውን የማያባራ የአየር ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።
ከአየር ጥቃት በተጨማሪም እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ሰርጥ አስገብታለች።
የእስራኤል ወታደሮች በሰሜናዊቷ ጋዛ ቤት ሃኖን ተከማችተዋል።
ወደ ደቡባዊ ጋዛም በተወሰነ መልኩ እየገፉ ይመስላል።
እስራኤል እና ጋዛን በምታዋስነው የድንበር ከተማ ስዴሮትም የነበረው የቢቢሲ ጋዜጠኛ በባለፉት ቀናት የከባድ መሳሪያ ተኩሱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ታዝቧል።
በጋዛ ላይ እየተተኮሰ ያለው ከባድ መሳሪያ አያባራም።
የስዴሮት ከተማ ሰው ዝር የማይልባት ሆናለች።
በርካታ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል ወይም እንዲወጡ ተደርገዋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ላይ የሚያደርገውን ጥቃት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም እያስታወቀ ነው።
በባለፉት ሁለት ቀናት ከጋዛ የወጡ ቪዲዮዎችም የከፋ የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸውን አሳይተዋል።
ነገር ግን የስልክ እና ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ መቋረጡንም ተከትሎ ምን እንደተከናወነ ለማወቅ ፈታኝ አድርጎት ነበር።
በደቡባዊ ጋዛ ከሚገኘው ዋና መስሪያ ቤታቸው ጋር በሳተላይት ስልክ መገናኘት የቻሉትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቢቢሲ ያነጋገረ ሲሆን የእርዳታ ስራቸውን ከሚከታተሉት የአካባቢ ቢሮዎች ጋር መገናኘት እንዳልቻሉም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት እርዳታ ሙሉ በሙሉ የታገደ ሲሆን ቢሮዎቹም በምን ሁኔታ ላይ እንደሆኑም ማወቅ አልተቻለም።
የእስራኤል የአየር ጥቃት በሰሜናዊ ጋዛ ላይ ቢያተኩርም የጋዛ ሰርጥ 45 ኪሎሜትር ርዝማኔ ብቻ ያላት በመሆኑ ፍንዳታውን በዙሪያው እና በሁሉም አካባቢ መስማት ይቻላል።
የእስራኤል ጦር ሐማስ የሚጠቀምባቸውን ዋሻዎች ለማጥራት እየሞከረ የሚመስል ሲሆን ልዩ ኃይሎችም ለአየር ጥቃቱ ኢላማ የሚደረጉ ስፍራዎችንም እየመረጡ ሳይሆን አይቀርም።
ታንኮች በቀን ብርሃን የበለጠ ተጋላጭ ሊሆኑ ስለሚችሉ እስራኤል የተወሰኑትን ልትመልሳቸው ትችላለች።
ነገር ግን የከባድ መሳሪያ ጥቃቶች እንደቀጠለ ነው።
የእግረኛ ጦሯ ማጥቃት ጀምሯል? እስራኤል ወታደሮቿን ስታከማች እና ከ300 ሺህ በላይ ተጠባባቂ ጦሯን ስትጠራ በሁሉም ግንባር የጋዛ ወረራ የምትፈጽም እንደሆነ ታስቦ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ጦሩ እያከናወነ ያለው ቀስ በቀስ የመጠራረግ ስራ ይመስላል።
የእስራኤል ጦር የምድር ላይ ጥቃቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥቶ ያስታወቀ ሲሆን ሐማስ ለፈጸመው ጥቃትም “ምላሽ” እንደሆነም የጦሩ መሪዎች ሲናገሩ ተደምጧል።
ምናልባትም የተራዘመ ወረራ ወይም የመሬት ጥቃት ሊባል ይችላል።
ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻም ነው።
እስራኤል በመሬት ላይ የምታደርገው ጥቃት በርካታ የፍልስጥኤም ሰላማዊ ዜጎችን እንደሚገድልም እርግጥ ነው።
በርካታ ፍልስጥኤማውያንን በገደሉ ቁጥር በመካከለኛው ምስራቅ፣ በእስራኤል ወዳጆችም ሆነ ጠላቶቿ ዘንድ ቁጣን ማስነሳቱ የማይቀር ነው።
ጦርነቱ ይዛመታል ለሚለው ዋስትና ባይሰጥም ነገር ግን አለመረጋጋት በማይለየው በቀጣናው የበለጠ ሁከትን መፍጠሩ የማይቀር ነው።












