“እኛ ነን ቤተ ክርስቲያን” መንግሥትን በሚደግፉ የሃይማኖት አባቶች ላይ ያመጹት የኬንያ ወጣቶች

ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ እየታደሙ ያሉ ወጣቶች

የኬንያ ወጣቶች ቆርጠዋል።

ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ከሥልጣን እንዲወርዱ እየጠየቁ ያሉት ተቃዋሚዎች መንግሥትን እየደገፉ ነው በሚባሉ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናት ላይ ተነስተውባቸዋል።

የግብር ጭማሪዎችን የያዘው የፋይናንስ ሕግ እንዲሰረዝ መጠየቅ መነሻ ሆኖ ሩቶ እንዲወርዱ እየጠየቀ ያለው የወጣቶች ተቃውሞ ለአብያተ ክርስቲያናቱ የማንቂያ ደወል ሆኗል።

በኬንያ የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ሩቶን ጨምሮ ከ80 በመቶ በላይ ሕዝቧ የክርስትና እምነት ተከታዮች ናቸው።

ወጣቱ ይህንን የሕዝብ መሠረት ያለው ኃይለኛ ተቋም እያንቀጠቀጡ ይገኛሉ።

ወጣቶቹ አብያተ ክርስቲያናት ለመንግሥት ወግነዋል እንዲሁም ለፖለቲካ መጠቀሚያነት ውለዋል እያሉ በመክሰስም ላይ ይገኛሉ።

በቅርቡ አንድ እሁድ ከሰዓት በኋላ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለተፈጠረው ችግር ምላሽ ሰጥተዋል።

በሕዝባዊ ተቃውሞ በፖሊስ የተገደሉትን ወጣቶች ለማሰብም በናይሮቢ እና በአካባቢው ያሉ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ልዩ የጸሎት ሥነ ሥርዓት አካሂደው ነበር።

የሞቱትን ነፍስ እንዲያሳርፍ ለመጸለይ በተካሄደው መርሃ ግብር ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ ሆሊ ፋሚሊ ባሲሊካ ቤተ ክርስቲያን አቅንተው ነበር።

ከሳምንታት በፊት በዚሁ ቤተክርስቲያን የእሁድ ቅዳሴ በተቃዋሚ ወጣቶች መፈክር እንዲስተጎል ተደርጎ ነበር።

በአብዛኛው ጄኔሬሽን ዙመር (ጄንዚ) በተሰኘው ወጣት ትውልድ የሚመራው ይህ ተቃውሞ በቤተ ክርስቲያንም ላይ ቅዳሴን በማቋረጥ ያለውን ተቃውሞ አሰምቷል።

ቤተ ክርስቲያኗ ወጣቶቹ መንግሥት ሊጥለው ያቀደውን የግብር ጭማሪ አስመልክቶ ያነሱትን ተቃውሞ እየደገፈች አይደለም በሚልም ነበር ተቃውሟቸውን ያሰሙት።

ከሳምንታት በኋላ በቅርቡ በነበረው ሟች ወጣቶችን ለማሰብ በነበረው የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ጳጳስ ሲሞን ካሞሞዬ ወጣቶቹን “ሰምተናችኋል” በማለት ለማሳመን ሞክረዋል።

“ወጣቶች እንደመሆናችሁ መጠን አንዳንድ ጊዜ በቤተክርስቲያኗም ቅር እንደምትሰኙ አውቃለሁ” ብለዋል።

“እናንተን ለማገልገል ቃል ኪዳናችንን ማደስ እንፈልጋለን። ተሳሰስተናል። እንደ ቤተ ክርስቲያን ስላሳዘንናችሁ አምላክ ይቅር ይበለን” በማለት ጳጳሱ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ወጣቶቹ አላማቸውን እና ህልማቸውን ለማሳካት እንዲታገሱ፣ በቤተ ክርስቲያኗ እንዲመሩ እና በተቃውሞው ወቅት ለተፈጸሙ ኃጢያቶችም ንስሐ እንዲገቡ አሳስበዋል።

“እናንተን፣ ወጣቶቻችንን ማጣት አንፈልግም” ሲሉ ጳጳሱ በሚያስገርም ቅንነት ተናግረዋል።

የኬንያ ህዝባዊ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, EPA

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክለውም “የካቶሊክ ጳጳሳት ይህንን ትውልድ ማጣት በጣም ያሳስባቸዋል” በማለት ሰላማዊ እንዲሆኑ እና ሕይወታቸውን እንዲጠብቁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ቅዳሴው በመንፈሳዊ ዝማሬ ታጅቦ የነበረ ሲሆን፣ በመጨረሻም ምዕመናኑ የኬንያን ሰንደቅ ዓላማ ካውለበለቡ በኋላ ዝግጅቱ ተጠናቀቀ።

በስፍራው ተገኝተው የነበሩ ምዕመናን ቤተ ክርስቲያኗ ወጣቶቹን ለማናገር ያደረገችውን ጅማሮ እንደበጎ ቢያዩትም እርምጃው ግን የዘገየ ነው ብለዋል።

“ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ ወጣቶቹ መቁረጣችውን እየተገነዘበች እንደሆነ ይሰማኛል” ሲል ዬቦ የተሰኘ በተቃውሞው ላይ ተሳታፊ የነበረ ወጣት ገልጿል።

“ቤተ ክርስቲያኗ ከጎናችን እንዳልነበረች ይሰማናል” የሚለው ዬቦ “ወጣቶቹ በጽናታቸው ቀጥለዋል። አሁን ባለው የምጣኔ ሀብት ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያኗ በበለጠ ወጣቱ ለውጥ ማምጣት ችሏል። ፕሬዚዳንቱም ከቤተ ክርስቲያኗ በላይ ለወጣቱ ያለው ግምት ከፍተኛ መሆኑንም አይተናል” ይላል።

የአብያተ ክርስቲያናት ማኅበራት በግብር ጭማሪዎች ላይ ዘመቻ ቢያካሂዱም ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶን ፓርላማ ያጸደቀውን የፋይናንስ ሕግ ውድቅ እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው ለአደባባይ ተቃውሞ የወጣው ወጣት ነው።

ይህ ብቻ አይደለም።

የጄንዚ ተቃዋሚዎች በቤተ ክርስቲያኗ እና በፖለቲካ ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት የጠበቀ ነው በሚልም እያወገዟቸው ይገኛሉ።

ለወጣቶቹ መታሰቢያ ከነበረው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ጎን ለጎን የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች ወደ ፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ቤት፣ ስቴት ሐውስ በተቃውሞው ወቅት ጭምር ያደርጓቸው ስለነበሩ አጠራጣሪ ጉብኝቶች እየተናገሩ ነበር።

“ፕሬዚዳንቱ ቤተ ክርስቲያኗን በገንዘብ እየገዛቸው ነው ብለን እናምናለን” ሲልም ሜሻክ ምዌንድዋ የተሰኘ ወጣት ይናገራል።

አክሎም “የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ከመንግሥት የሥራ አስፈጻሚዎች እና ባለሥልጣናት ጋር የፖስታ እሽጎች ይዘው ታይተዋል” የሚለው ሜሻክ “እናም እንደ ወጣት የምንፈልገው ያ አይደለም፤ አሁን ጊዜው የለውጥ ነው” ይላል።

ወጣት ተቃዋሚዎቹ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በተያየዘ አንድ ለውጥ ማስገኘት ችለዋል።

ይህም “ሃራምቤ” የሚሰኝ ሲሆን፤ ፖለቲከኞች ለቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ገንዘብ የሚሰጡበት ሁኔታ ነው። እንዲህ ዓይነት የፖለቲከኞች የገንዘብ ልገሳ በምላሹ እሁድ ጥዋት በሚደረጉ የቤተ ክርስቲያኗ ፕሮግራሞች ላይ ድጋፍ እና ተጽእኖ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ናቸው።

ፓርላማን እንቆጣጠር ‘ኦኩፓይ ፓርላመንት’ በሚል የፖለቲካ ማዕከሉ ላይ ያለመው የወጣቱ ተቃውሞ ቤተ ክርስቲያኗንም እንቆጣጠር ‘ኦኩፓይ ቸርች’ የሚል መፈክርም ነበረው።

በቤተ ክርስቲያን ስፖንሰር በተደረገ ዝግጅት ላይ የፕሬዚዳንት ሩቶ መገኘትን አንዳንዶች በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ወጥተው ነበር። ሩቶም ይህንን በማክበር ሳይገኙ ቀርተዋል።

“የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የአምልኮ ቦታዎችን መድረክ ለፖለቲካ አላማ ልንጠቀም አይገባም። ትክክል አይደለም” ሲሉም ሩቶ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተነሳባቸው በኋላ የተለያዩ ማሻሻያዎች እያደረጉ ያሉት ሩቶ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የመንግሥት ሠራተኞች ሕዝባዊ የበጎ አድራጎት ልገሳ እንዳይሰጡ እገዳ አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም መዋቅሩ የተስተካከለ እና ግልጽነትን የሚያሳይ የልገሳ መመሪያ እንዲያዘጋጅም ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ራሳቸው የቤተ ክርስቲያንን መድረክ ለምርጫ ቅስቀሳ በመጠቀም እና የሚደረጉ ልገሳዎችንም ለፖለቲካ መጠቀሚያነት የሚያደርገው ባህል አካል ናቸው።

“ፖለቲካዊ መልዕክታቸው መነሻ የነበረው በቤተ ክርስቲያኗ ነው። ይህም ህዝቡ የክርስቲያን መንግሥት እንዳላቸው እንዲሰማቸው አድርጓል” በማለት የኬንያ ብሔራዊ የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ቄስ ክሪስ ኪንያንጁይ ያስረዳሉ።

ሩቶ ሲጠቀሙበት የነበረው ክርስቲያናዊ ትርክት በርካታ ፓስተሮች እሳቸውን ተጠያቂ ለማድረግ እንዳስቸገራቸው የሚናገሩት ቄስ ክሪስ እንዲያውም እነዚህ የሐይማኖት አባቶች “ራሳቸውን የአስተዳደሩ ባለ አክሲዮኖች አድርገው ነው የሚያዩት” ይላሉ።

“ፕሬዚዳንቱ ከቤተክርስቲያኗ አትሮኖስ ሆነው ነው የሚናገሩት። አትሮኖስ (መንበር) ማለት እኮ የማትጠየቅበት ስፍራ ነው። ስለዚህ ይህንን ማድረጋቸው በኬንያ ፖለቲካ እና ቤተ ክርስቲያን ኃያል ሰው አድርጓቸዋል። ወጣቱ ግን በመንግሥት እና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ልዩነት እያየነው አይደለም በማለት እየጠየቋቸው ነው” ይላሉ የሃይማኖት አባቱ

ቢቢሲ ይህንን አስመልክቶ የኬንያ መንግሥትን ምላሽ ቢጠይቅም ቃለ አቀባዩ በአሁኑ ወቅትም ምንም ማለት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ቃለ አቀባዩ ይህንን የተጠየቁት ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ሩቶ ሚኒስትሮቻቸውን በማባረር የሰጡትን ምላሽ አስመልክቶ እየሰጡት በነበረው መግለጫ ላይ ነው።

የኬንያ ወጣቶች ያስነሱት ህዝባዊ ተቃውሞ በአገሪቱ ላይ ያለውን የኃይል መዋቅር እየቀየረው ይገኛል፥

በርካታውን የህዝብ ቁጥር የሚይዘው ይህ ትውልድ በማይተነበይ መልኩ አዳዲስ የመታገያ ስትራቴጂዎችን እየተከተሉ ይገኛሉ።

በዚህም ምክንያት ፕሬዚዳንቱም ሆነ አብያተ ክርስትያናቱም ወጣቶቹን ለመስማት ተገደዋል።

“እኛ ቤተ ክርስቲያን ነን” ነበር ምላሹ ሚቸሊ ምቡጓ በባሲሊካ ቤተ ክርስቲያን የነበረው ቅዳሴ ሲቋጭ ያለው

“ቤተ ክርስቲያኗ እኛን የማትደግፈን ከሆነ እኛም እንርቃለን። እኛ ከሌለን ቤተ ክርስቲያን የለችም። ስለዚህ ቅሬታችንን ማዳመጥ አለባቸው። ምክንቱም እኛ ነን ቤተ ክርስቲያኗ” ይላል።

ቄስ ክሪስ በወጣቶቹ ተቃውሞ ያዩት ነገር ቢኖር ያሉት የማህበራዊ ውሎች መላላትን ነው።

በተለይም ተቃውሞው በተቀጣጠለበት ወቅት ጉባዔው ኬንያ የሱዳንንን መንገድ ትከተል ይሆን የሚል ስጋት እንደነበራቸው አምነዋል።

በሱዳን የነበረው የወጣቶች አብዮት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተቀልብሶም መጨረሻም አገሪቷ ደም አፋሳሽ ወደ ሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ገብታለች።

“ፕሬዚዳንቱ ይህንን ቀውስ ማክሸፍ በመቻላቸው ተደስተን ነበር። ያንን የፋይናንስ ረቂቅ ህግ ቢፈርሙ ኖሮ ምን እንደሚፈጠር ማን ያውቃል? “ ሲሉም ይጠይቃሉ።

ቄስ ክሪስ የአብያተ ክርስቲያናቱ ጉባኤ በፋይናንስ ረቂቁ ላይ ዝምታን ተከትሎ እንደነበር አምነው ከዚህ በኋላ ግን የህዝቡን ጥያቄ ወደፊት በማምጣት፣ አገዛዙን በማረም፣ ለማህበረሰቡ ድምጽ ለመሆን እንደሚሰሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።

“በአንድ መንገድ ይህ ትውልድ የአምላክን ስራ እየሰራ እንደሆነ እናያለን። እናም ይህ ሁኔታ በርካታ ፓስተሮች እንዲነቁ ያደረገ ይመስለኛል” ብለዋል።