ካማላ ሃሪስ በይፋ የዴሞክራቶች እጩ ሆኑ

ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በይፋ የዴሞክራቶች የፕሬዝዳንት እጩ ሆነዋል።

ሃሪስም “እጩ በመሆኔ ክብር ተሰምቶኛል” ብለዋል።

በቀጣይ ወር ቺካጎ ውስጥ የዴሞክራቶች ብሔራዊ ጉባዔ ይካሄዳል።

ሃሪስ የመጀመሪያዋ ጥቁርና ደቡብ እስያዊ የዘር ግንድ ያላቸው ሴት የፕሬዝዳንት እጩ ናቸው።

ዶናልድ ትራምፕን ካሸነፉም የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ራሳቸውን ከውድድሩ ካገለሉ በኋላ ሃሪስ ያለተፎካካሪ እጩ ሆነዋል።

ባይደንን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች ድጋፋቸውን ለሃሪስ ሰጥተዋል።

በይፋ እጩ የሆኑት የ2,350 ተወካዮችን ድጋፍ ካገኙ በኋላ ነው። ይህ ቁጥር እጩ ለመሆን የሚያበቃ ነው።

ሃሪስ በይፋ እጩ ከሆኑ በኋላ በስልክ “አሜሪካ በምትሰጠው ተስፋ እናምናለን። የምርጫ ቅስቀሳችንም እሱን ይመለከታል” ብለዋል።

“ሁላችንም አብረን ነን። ቀላል አይሆንም። ግን እናሳካዋለን” ሲልም አክለዋል።

ካሉት አጠቃላይ 3,923 የዴሞክራት ተወካዮች መካከል 99% ድምጻቸውን ለሃሪስ ይሰጣሉ።

ፕሬዝዳንቶችና ምክትል ፕሬዝዳንቶች የሚመረጡት በፓርቲያቸው ጉባዔ ነው።

የ59 ዓመቷ ሃሪስ የተወለዱት በኦክላንድ፣ ካሊፎርንያ ነው። ከምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ፓርቲው የፕሬዝዳንት እጩ ሲያቀርብ በ200 ዓመት ውስጥ የመጀመሪያው ነው።

በሳን ፍራንሲስኮ ፖለቲከኛ የነበሩት ሃሪስ የካሊፎርያ ዐቃቤ ሕግ ሆነውም ሠርተዋል። ከዚያም ሴናተር ሆነዋል።

ባይደን ከውድድሩ ራሳቸውን ከማግለላቸው በፊት ስለ ዕድሜያቸው ጉዳይ ጥያቄዎች ቢኖሩም እንኳን ከፓርቲው 99% ድጋፍ አግኝተው ነበር።

የ81 ዓመቱ ባይደን ከትራምፕ ጋር ባደጉት ክርክር ባሳዩት ያነሰ ብቃት ፓርቲው ጫና አሳድሮባቸው ከውድድሩ ወጥተዋል።

የፓርቲ ተወካዮች ምክትል ፕሬዝዳት የማይመርጡ ሲሆን፣ ሃሪስ ምክትል ፕሬዝዳንታቸውን ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን እንዲሁም የተወሰኑ ሪፐብሊካኖች ባይደን በሃሪስ በመተካታቸው ቅሬታ አሰምተዋል።

ጋዜጣዊ መግለጫ ሳይሰጡና ቃለ ምልልስ ሳያደርጉ የፓርቲ እጩ ሆነው በመቅረባቸው ነው ቅሬታቸውን የገለጹት።

“መፈንቅለ መንግሥት ነው” ሲሉ የገለጹትም አሉ።

ሆኖም ግን ሃሪስ የምርጫ ቅስቀሳቸውን በሰፊው ገፍተውበታል። በሐምሌ ወር ከ310 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው ይፋ አድርጓል።

ገንዘብ ከለገሱ መካከል ሁለት ሦስተኛው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ገንዘብ የሰጡት።

ትራምፕ ባለፈው ወር ማሰባሰብ ከቻሉት 138 ሚሊዮን ዶላር የካማላ ሃሪስ በእጥፍ ይበልጣል።