ቪፒኤን ምንድነው? እንዴትስ መጠቀም ይቻላል?

ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትዎርክ (ቪፒኤን)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት መንግሥታት በኢንተርኔት ላይ ገደቦችን ሲጥሉ ተጠቃሚዎች ክልከላዎቸን ለማለፍ ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትዎርክ (ቪፒኤን) ለመጠቀም ይገደዳሉ።

በኢትዮጵያም ባለፉት ዓመታት የኢንተርኔት ግንኙነት ላይ ገደብ ሲጣል የቪፒኤን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እንደ ፌስቡክ፣ ሜሴንጀር፣ ቲክቶክ እና ቴሌግራም ባሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እና መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ላይ ገደብ መጣሉን ተከትሎ የቪፒኤን ተጠቃሚዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ይታመናል።

በዓለም ዙሪያ የኢንትርኔት መዘጋት እና የተወሰኑ አገልግሎቶች እቀባ በሚያጋጥሙባቸው አካባቢዎች ኢንትርኔትን ለመጠቀም የሚያስችሉ ቪፒኤን የሚባሉትን መተግበሪያዎች አጠቃቀም የሚከታተለው ‘ቶፕ10ቪፒኤን’ የተባለው ድረገጽ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቪፒኤን የመጠቀም ፍላጎት እንዳለ ገልጿል።

ድረገጹ ያለፉትን 28 ቀናት የቪፒኤን ፍላጎት በዛሬ ዕለት አርብ እኩለ ቀን ድረስ ካለው ጋር በማነጻጸር ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የቪፒኤን ፍላጎት በ414 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ ይህም ከአማካዩ የቪፒኤን ፍላጎት በ1,430 ፐርሰንት ማሻቀቡን አመልክቷል።

ይህ በኢትዮጵያ የቪፒኤን መጠቀሚያ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ ምክንያት የሆነው፣ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ሃይማኖታዊ ቀውስ ተከትሎ ባለሥልጣናት በፌስቡክ፣ በቴሌግራም እና በቲክቶክ ላይ እገዳዎችን መጣላቸውን ተከትሎ መሆኑን ድረገጹ ገልጿል።

ቪፒኤን የሚሠራው እንዴት ነው?

ቨርቿል ፕራይቬት ኔትዎርክ (ቪፒኤን) የኢንርኔት ደኅንነት የሚሰጥ፣ ግለኝነትን የሚጠብቅ እና ነጻነት የሚሰጥ መተግበሪያ ነው።

ሰዎች የቪፒኤን መተግበሪያዎችን ወይም ሶፍትዌሮችን በስልካቸው እና በኮምፒየተሮቻቸው ላይ መጫን ይችላሉ።

የቪፒኤን መተግበሪያ በስልክዎ ወይም በኮምፒውተርዎ መካከል እና በሌላ ቦታ በሚገኝ ከመረጡት የቪፒኤን ሰርቨር ጋር ግንኙነት ይፈጥራል።

በዚህም ቪፒኤኑ የተጠቃሚውን የኢንርኔት አድራሻ (አይፒ አድሬስ) እና መገኛ ቦታ በመቀየር ክልከላዎችን አልፎ ለመጠቀም ያስችላል።

ቪፒኤን መጠቀም ወይም መጎብኘት የማይቻሉ ድረ ገጾችን ለማየት፣ መተግበሪያዎች እንዲሠሩ ለማደረግ እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች (እንደ ኢትዮቴሌኮም ያሉ) ተጠቃሚዎች የሚጎበኙት ድረ ገጽ መረጃ እንዳይኖራቸው ያደርጋል።

ክፍያ የማይጠየቅባቸው ቪፒኤኖች?

ፎርብስ በብዙ ቪፒኤኖች ላይ ፍተሻዎችን አድርጌ ለይቻለሁ ያላቸውን ቪፒኤኖችን አጋርቷል።

የዘርፉ ባለሙያዎች በነጻ አገልግሎት ከሚሰጡት ቪፒኤኖች ይልቅ የሚከፈለባቸው መተግበሪያዎች ፈጣን እና ደኅንነታቸው የተረጋገጡ ናቸው ይላሉ።

ፎርብስ በእአአ 2023 በነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ቪፒኤኖችን ፈትሾ ምርጥ ያላቸውን መተግበሪዎች ይፋ አድርጓል።

የተሻለ ደኅንነትን የሚሰጡ፣ ግለኝነትን የሚያረጋግጡ እና አስተማማኝ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ካላቸው መተግበሪያዎች መካከል ፕሮቶን ቪፒኤን (Proton VPN)፣ ዊንድክራብ (Windcribe)፣ ፕሪቫዶ ቪፒኤን (Privado VPN) እና ሆትሰፖት ሺልድ (Hotspot Shield) ተጠቃሽ ናቸው።

ፎርብስ እአአ 2023 ላይ ክፍያ ከሚጠየቁባቸው ቪፒኤኖች መካከል የተመረጡ ናቸው ካላቸው መካከል መተግበሪያዎች መካከል ደግሞ ፕራይቬት ኢንተርኔት አክሰስ (Pricate Internet Access)፣ ኤክስፕረስቪፒኤን (ExpressVPN)፣ ኖርድቪፒኤን (NordVPN) እና ሳይበርጎስት (CyberGhost) ይጠቀሳሉ።

የቪፒኤን አጠቃቀም

ቪፒኤን እንዴት መጠቀም ይቻላል?

ቪፒኤንን ካላይ በምስሉ ላይ በተመላከተው መሠረት ሦስት ቀላል ቅድመ ተከተሎችን በመከተል መጠቀም ይቻላል።

ቪፒኤን በስልክ መጠቅም የምንፈልግ ከሆነ፤ አንድሮይድ ተጠቃሚዎች ወደ ጉግል ፕሌይ፣ የአይፎን ተጠቃሚዎች ወደ አፕስቶር፣ የሁዋዌ ተጠቃሚዎች ደግሞ ወደ አፕጋለሪ በማቅናት የመረጡትን ቪፒኤን በማውረድ መጫን።

በመቀጠል መተግበሪያው ለሚጠይቃቸው ጥያቄ ምላሽ ይስጡ። ለምሳሌ ካለይ በታያየው ምስል (መሃል) ሆትሰፖት ሺልድ ከተጫነ በኋላ በክፍያ ወይም የነጻ አገልግሎት አማራጭን ይሰጣል።

የነጻውን አማራጭ የሚመርጡ ከሆነ ፍጥነቱ ዝግ ያለ እና ማስታወቂያ ያሚያሳይ አገልግሎት ያገኛሉ።

በመጨራሻም የቪፒኤን አገልግሎት ለማስጀመር የማብሪያ እና ማጥፊውን ምልክት መጫን ነው።