የሞት ፍርድ ተፈጻሚ የሚሆንበት አሜሪካዊ ልጁ ግድያውን እንዳታይ ፍርድ ቤት ወሰነ

የሞት ፍርድ ተፈጻሚ የሚሆንበት አሜሪካዊ የ19 ዓመት ልጁ ግድያው ሲከናወን እንዳትታደም ፍርድ ቤት ወሰነ።

ዳኛውም ዕድሜዋ ትንሽ ነው ሲሉም የሚዙሪን ህግ ጠቅሰዋል።

ኬቨን ጆንሰን በአውሮፓውያኑ 2005 ፖሊስ በመግደሉ የሞት ቅጣት የተፈረደበት ሲሆን በመጪው ማክሰኞም ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።

ኬቨን ጆንሰን በወቅቱም 19 ዓመቱም ነበር።

ግለሰቡ የሞት ቅጣቱ ተግባራዊ በሚሆንበት እለት ሴት ልጁ ክሆሪ ራሚ እንድትገኝ ጠይቋል።

የአሜሪካ የሲቪል ነጻነቶች ህብረት በታዳጊዋ ስም የአስቸኳይ ጊዜ ጥያቄ አቅርቧል።

የግዛቲቱ ህግ የግለሰቧን ህገ መንግስታዊ መብቶቿን ጥሷል ብሏል ህብረቱ።

በሚዙሪ ህግ መሰረት ከ21 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው የሞት ፍርድ ሲፈጸምበት እንዳይታደም ይከለክላል።

ይህ ህግ ምንም ዓይነት የደህንነት ዓላማ የለውም ብለዋል።

የ37 ዓመቱ ኬቨን፣ ልጁ ክሆራ የሁለት ዓመት ልጅ እያለች ነበር የታሰረው።

አባትና ልጅ በባለፉት ዓመታት በጉብኝት፣ በስልክ ጥሪዎች፣ በደብዳቤዎች እና በኢሜይሎችም ግንኙነታቸውን ማጠናከር ችለዋል።

ባለፈው ወር አዲስ የተወለደች ልጇንም ወደ እስር ቤት ይዛ መጥታ በእስር ላይ ያለ አያቷንም ጎብኝታለች።

“ከአባቴ ጋር በመጨረሻዎቹ ጊዜያት መሆን ባለመቻሌ ልቤ በኃዘን ተሰብሯል” ስትል ልጁ በሰጠችው መግለጫ ተናግራለች።

አባቷ በእስር ቤት ራሱን ለማስተካከል በርካታ ጥረት እንዳደረገ እና እየጸለችም እንደሆነ ተናግረለች። የሚዙሪም ገዥ ምህረት እንዲያደርግም ጠይቃለች።

ኬቨን የሶስት ልጆች አባት የሆነውን የሚዙሪ ፖሊስ ዊልያም ማኬንቴን በጥይት አቁስሎ ህይወቱ በማለፉ የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል።

የኬቨን ጠበቆች ህይወቱ እንዲተርፍ ይግባኝ ጠይቀዋል። ምንም እንኳን ጥፋቱን ባይክዱም ዘረኝነት በሞት ቅጣት ብያኔው ላይ ሚና ነበረው ይላሉ።