ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎች ‘አንፈተንም’ ብለው ከፈተናው መውጣታቸው ተገለጸ

በአገሪቱ ከዚህ በፊት ሲሰጡ ከነበሩት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች በተለየ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካሄደው ፈተና ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎች አንፈተንም በማለት ከፈተና ማዕከላት መውጣታቸው ተገለጸ።

በሁለት ዙር ተከፍሎ ከሚሰጠው የ2014 ዓ.ም. አገር አቀፍ ፈተና ውስጥ ለማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ከሰኞ መስከረም 30/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሰጥ የነበረው ፈተና መጠናቀቁን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ለምዘና በተቀመጡበት ፈተና፣ ከአራት የፈተና ማዕከላት ወደ 13 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ፈተናውን አንወስድም በማለት ሳይፈተኑ መቅረታቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ከዚህ በፊት ያጋጠሙ የፈተና ስርቆትና ኩረጃን ለመከላከል በሚል የትምህርት ሚኒስቴር ተግባራዊ ባደረገው በዚህ የፈተና ሂደት፣ ተማሪዎች በመላው አገሪቱ በሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በመሆን ፈተናውን እንዲወስዱ ተደርጓል።

በመንግሥት በኩል ለተማሪዎቹ ትራንስፖርት፣ ምግብና መኝታን በማቅረብ ፈተናው በጥብቅ ቁጥጥር ስር መካሄዱን የተነገረ ሲሆን፣ በአንዳንድ ስፍራዎች ችግሮች መከሰታቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።

ከእነዚህም መካከል በፈተናው የመጀመሪያ ቀን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኝ የመሸጋገሪያ ድልድይ ተደርምሶ በደረሰ አደጋ የአንድ ተማሪ ሕይወት ሲያልፍ፣ በርካታ ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው በዋናው ግቢ የመጀመሪያው ዕለት ፈተና ሳይሰጥ ቀርቶ ነበር።

በተከሰተው አደጋ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸውም ሆነ በተፈጠረው ሁኔታ ፈተና ሳይወስዱ የቀሩ ተማሪዎች በሁለተኛ ዙር ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋል ተብሏል።

ይህንን የመጀመሪያው ዙር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሂደትን በተመለከተ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአራት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ከተመደቡ ተማሪዎች መካከል ሳይፈተኑ የቀሩ እንዳሉ አመልክተዋል።

በዚህም በአማራ ክልል በመቅደላ አምባ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በባሕር ዳር እና በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች መፈተን ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል 12 ሺህ 787 ተማሪዎች የተወሰኑትን ፈተና ወስደው ወይም ሙሉ ለሙሉ ከፈተናው እራሳቸውን አግልለዋል።

እነዚህ ተማሪዎችም 1,700 ከመቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ መካነ ሰላም ካምፓስ፣ 1,226 ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ፣ 2,711 ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ እና 7,150 ከደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ የወጡ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አመልክቷል።

የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ክስተት “ከትምህርት ሥርዓቱ ያፈነገጠ ነው” ያለ ሲሆን፣ አንፈተንም በማለት ከፈተና ማዕከላቱ ለቀው የወጡ ተማሪዎች በፈቃዳቸው ያደረጉት በመሆኑ ሌላ የፈተና ዕድል እንደማይኖራቸው ተገልጿል።

በተፈጠረው ግርግር እና በሌሎች ጫና ከፈተናው አቋርጠው ወጥተው ከነበሩት ተማሪዎች መካከል ፍላጎቱ ያላቸውን ከሰባት ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ፈተናው መመለሳቸውን ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በተለይ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኃይል በተቀላቀለበት ሁኔታ ፈተናውን ለማስተጓጎል በፈጠሩት ግርግር የአንድ ተማሪ ሕይወት ሲያልፍ በፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።

ሚኒስቴሩ ፈተና ለማስተጓጎል ሙከራ ባደረጉ ተማሪዎች ላይም አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ፈተና የመሠረዝ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።

በመጀመሪያው ዙር የ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ ተብለው ከተጠበቁት 595 ሺህ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ውስጥ 586,541 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በመውጣት ለውጥ ለማድረግ እየሰራባቸው ካሉ ዘርፎች ዘርፎች አንዱ ትምህርት ነው ያለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና አሰጣጥ በትምህርት ላይ እየመጣ ላለው ለውጥ አንዱ ማሳያ ነው ብሏል።

ጨምሮም ተግባራዊ የሆነው አዲስ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ከዚህ በፊት በብልሹ አሠራር፣ በስርቆት እና በማጭበርበር ይደረግ የነበረውን የፈተና ሂደት በማስቀረት ሁሉም ተማሪ እኩል የሚመዘንበት ዕድል ይፈጥራል ብሏል።

በተለየ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካሄድ ላይ ባለው የ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና የተሳካ እንዲሆን በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ መንግሥት በመመደብ፣ በ160 ማዕከላት ከአንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች እና ፈታኝ መምህራን በፈተናው እንዲሳተፉ መደረጉ ተጠቅሷል።

በቀጣይ ሳምንት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በተመሳሳይ ሂደት ፈተናው እንደሚሰጣቸው የትምህርት ሚኒስቴር መረሃ ግብር ያመለክታል።