ቻይና ታይዋንን በከበባ ለመዝጋት የሚያስችላትን ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ ተነገረ

የቻይና ጦር ጄት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቻይና ጦር ጄት በምስራቅ ታይዋን አቅጣጫ

ቻይና ለሦስተኛ ቀን እያካሄደች ባለችው የጦር ልምምድ የታይዋን ደሴትን “በከበባ መዝጋት” የሚመሳሰል ተግባራዊ ልምምድ ማድረጓን ገለጸች።

ቻይና በዚህ ወታደራዊ ልምምድ ላይ አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ በመጠቀም ተዋጊ ጄቶችን ወደ ታይዋን ለማሰማረት የሚያስችላትን ልምምድ አድርጋለች።

ቻይና ሻንዶንግ የተባለው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧ በጦር ልምምዱ መሳተፉን የገለጸች ሲሆን፣ ታይዋንም በምሥራቃዊ ክፍሏ ጄቶች መመልከቷን ገልጻለች።

ቻይና ወታደራዊ ልምምዱን ቅዳሜ ዕለት ማድረግ የጀመረችው፣ የታይዋን ፕሬዝዳንት ሳይ ኢንግ-ዌን በካሊፎርኒያ ከአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ ጋር ከተገናኙ በኋላ ነው።

ታይዋን እራሷን እንደ ሉዓላዊ አገር የምትመለከት ሲሆን፣ ቻይና ግን የራሷ አማጺ ተገንጣይ ግዛት እንደሆነች እና አስፈላጊ ከሆነ በኃይል እንደምትጠቀልላት ስትገልጽ ቆይታለች።

ዛሬ ሰኞ ታይዋን በዙሪያዋ 70 የጦር አውሮፕላኖች እና 11 መርከቦች ደግሞ በባሕር ላይ ተሰማርተው እንደነበር እንዲሁም ተዋጊ ጄቶች ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በምሥራቅ በኩል ጥቃት የመፈጸም ልምምድ ሲያደርጉ እንደነበር ገልጻለች።

የቻይና ጦር ሠራዊት ሰኞ ዕለት በተካሄደው የጦር ልምምድ ላይ ሻንዶን የተባለችው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ መሳተፏን ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።

ጨምሮም ለልምምዱ እውነተኛ ጥይት ጥቅም ላይ መዋሉን እና “ወሳኝ ተብለው በተዘጋጁ ምስለ ኢላማዎች ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን በመፈጸም” ልምምድ ተካሂዷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጃፓንም የቻይና ወታደራዊ ልምምድ መካሄዱን አረጋግጣ፣ ከሻንዶንግ መርከብ ላይ በተነሱ አውሮፕላኖች የአየር ጥቃት ልምምድ ተደርጓል ብላለች።

ካለፈው አርብ ጀምሮ አስከ እሁድ ድረስም ተዋጊ ጄቶች እና ሄሊኮፕተሮች 120 ጊዜ ከአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧ ላይ ተነስተው ማረፋቸውን የጃፓን መከላኬያ ሚኒስቴር ገልጿል።

ዛሬ ሰኞ አሜሪካ ሚሳኤል አውዳሚ የሆነችውን ዩኤስኤስ ሚሊየስ የተባለች መርከብ ከታይዋን 1,300 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ወደሚገኘው የደቡብ ቻይና ባሕር አሰማርታለች።

ቻይና ግን ይህ የአሜሪካ መርከብ “በሕገ-ወጥ ሁኔታ ወደ ባሕር ክልሌ ጥሶ ገብቷል” ስትል፣ አሜሪካ ደግሞ የመርከቧ ተልዕኮ ዓለም አቀፍ ሕግን ያከበረ ነው ብላለች።

አሜሪካ፣ ቻይና ከታይዋኗ ፕሬዝዳንት ጉብኝት አንጻር ጸብ ከሚጭር ድርጊት እንድትቆጠብ በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ቆይታለች። ቻይናም ፕሬዝዳንቷ ከከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር የሚገናኙ ከሆነ “አጸፋዊ እርምጃ” እንደምትወስድ አስጠንቅቃ ነበር።

ቻይና ይህንን የጦር ልምምድ ማድረግ የጀመረችው የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ምክሮንን እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይንን ጨምሮ ከፍተኛ የውጭ አገራት ባለሥልጣናትን አስተናግዳ ከሸኘች በኋላ ነው።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ከጉብኝታቸው በኋላ በታይዋን የተነሳ በአሜሪካ እና በቻይና መካከል በሚፈጠረው ፍጥጫ ውስጥ አውሮፓ እንዳትገባ መናገራቸው ትችትን አስከትሎባቸዋል።

የቻይና የጦር ልምምድ የተጀመረው የታይዋን ፕሬዝዳንት በአሜሪካ እና በአካባቢው አገራት ያደረጉትን የ10 ቀናት ጉብኝት አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ነው።

የታይዋኗ ፕሬዝዳንት ሳይ ኢንግ-ዌን በአሜሪካ መንግሥት የሥልጣን ተዋረድ ውስጥ ሦስተኛው ሰው ከሆኑት ከአፈጉባኤ ኬቭን ማካርቲ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ የቀድሞዋ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በታይዋን ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ቻይና ታይቶ የማይታወቅ ወታደራዊ ልምምድ በታይዋን ዙሪያ አድርጋ ነበር።

በቻይና ሲካሄድ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የበላይነት ይዞ፣ የቻይና የቀድሞ መሪዎች ወደ ደሴቲቱ ካፈገፈጉበት ከአውሮፓውያኑ 1949 ጀምሮ የታይዋን ሕጋዊ ሰውነት አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል።

የአሁኑ የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በቅርቡ እንደተነጋሩት ታይዋንን ከቻይና ጋር “መልሶ ማዋሃድ ተግባራዊ መሆን አለበት” ብለው ተናግረዋል።