ቻይና በታይዋን አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓን ተከትሎ ጥንቃቄ እንድታደርግ በአሜሪካ ተጠየቀች

የቻይና የጦር መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ባለፈው ሳምንት የታይዋን ፕሬዝዳንት ታይ ኢንግ-ዌን አሜሪካን ከጎበኙ በኋላ ቻይና ለሁለተኛ ቀን የባህር ኃይል ልምምዶችን በታይዋን ዙሪያ በማድረጓ በአካባቢው ውጥረት ነግሷል።

ቤጂንግ ለታይፔ "ከባድ ማስጠንቀቂያ" በማለት በጠራችው ወታደራዊ ልምምድ ደሴቲቱን ከግምት ያስገባ የባህር እና የአየር ኃይል እምምድ እየተከናወነ ነው።

እሑድ ዕለት በርካታ የቻይና የጦር ጄቶች በደሴቲቱ ዙሪያ በረራ ማድረጋቸውንና ዘጠኝ መርከቦችም መታየታቸውን ታይዋን ገልጻለች።

የታይዋን ባለስልጣናት ያስቆጣው የቤጂንግ ወታደራዊ ልምምድ እስከ ሰኞ ድረስ ይቀጥላል።

በታይፔ የሚገኙ የመከላከያ ባለስልጣናት ቤጂንግ ታይ ቺን ወደ ዋሽንግተን አቅንተው ከአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ኬቨን ማካርቲ ጋር መገናኘታቸውን ለወታደራዊው ልምምድ እንደሰበብ አቅርበውታል ብለዋል። ይህም የአካባቢውን ሠላምን እና መረጋጋትን በእጅጉ ጎድቷል ሲሉ ገልጸዋል።

ቅዳሜ ዕለት አንድ የቻይና የጦር መርከብ ለታይዋን ቅርብ በሆነችው በፒንግታን ደሴት አቅራቢያ አንድ ዙር ተኩሷል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል አስነብቧል።

የባህር ዳርቻ ጥበቃን የሚመራው የታይዋን ውቅያኖስ ጉዳዮች ምክር ቤት ምንም እንኳን ትክክለኛ ቦታውን ባይገልጽም ከመርከቦቻቸው አንዱ የቻይናን የጦር መርከብ ሲከተል የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል አውጥቷል።

በቪዲዮው እንደሚታየው አንድ መርከበኛ ለቻይናው መርከብ በሬዲዮ "የክልሉን ሠላም፣ መረጋጋት እና ደህንነት በእጅጉ እየጎዳችሁ ነው። እባካችሁ በአስቸኳይ ዙሩና ውጡ። በዚህ ከቀጠላችሁ እርምጃ እንወስዳለን" ሲል ተደምጧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሌላ ቪዲዮ ደግሞ ዲ ሁዋ የተሰኘው የታይዋን የጦር መርከብ ከባህር ዳርቻ ጥበቃ መርከብ ጋር በመሆን ከቻይና መርከብ ጋር “ተፋጦ” ታይቷል።

የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር እሑድ ዕለት እንዳስታወቀው በ24 ሰዓታት ውስጥ 71 የቻይና ወታደራዊ አውሮፕላኖች እና ዘጠኝ መርከቦች የታይዋን ሰርጥን አቋርጠዋል።

ሰርጡ በቻይና እና በታይዋን ግዛት መካከል ኦፊሴላዊ ያልሆነ የመለያ መስመር ነው።

የአሜሪካ ባለሰልጣናት ዩናይትድ ስቴትስ "የቤጂንግን ድርጊት በቅርበት እየተከታተለች ነው።”

አሜሪካ ከታይፔ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጣ በ1979 ቤጂንግን ደግፋለች። ነገር ግን ራሷን የምትከላከልበትን መንገድ ለታይዋን ለመስጠት እራሷን በህግ አስራለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በተለያዩ አጋጣሚዎች ቻይና በደሴቲቱ ላይ ጥቃት ካደረሰች አሜሪካ ጣልቃ እንደምትገባ ተናግረው ነበር።

በረቡዕ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ታይ አሜሪካ ለሰጠችው “የማይናወጥ ድጋፍ” አፈ-ጉባዔ ማካርቲን አመስግነዋል። “የታይዋን ህዝቦች እንዳልተገለልን እና ብቻችንን እንዳልሆንን ለማረጋጋጥ ረድቷልም” ብለዋል።

የማካርቲ የመጀመሪያ ዕቅድ ወደ ታይዋን የመሄድ የነበረ ቢሆንም ከቻይና ጋር ያለውን እሰጥ አገባ ለማስቀረት ስብሰባውን በካሊፎርኒያ ለማድረግ መርጠዋል።

የቻይና መንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት እስከ ሰኞ ድረስ የሚቆየው ወታደራዊ ልምምዱ “በታይዋን ደሴት ዙሪያ ቅኝቶችን እና እንቅስቃሴዎችን በአንድ ጊዜ ያደራጃል። ሁሉንም አቅጣጫም የመከላከያውን አቀማመጥ ይቀርፃል” ብለዋል።

የቻይና ጦር "ረጅም ርቀት ሮኬቶች፣ የባህር ኃይል መሣሪያዎች፣ የጀልባ ሚሳኤሎች፣ የአየር ኃይል ተዋጊዎች፣ ቦምብ ጣዮች እና ነዳጅ አቅራቢዎች" አሰማርቷል።

በቻይና የእርስ በርስ ጦርነት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የበላይነት በማግኘት የሀገሪቱ ገዢዎች ከ1949 ጀምሮ ወደ ደሴቱ ለማፈግፈግ መገደዳቸውን ተከትሎ የታይዋን ሁኔታ አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ሀገር የምትቆጥር፣ የራሷ ሕገ መንግሥትና መሪዎች ያላት ሆናለች። ቻይና ግን እንደ ተገነጠለች ግዛቷ የምትመለከታት ሲሆን አስፈላጊ ከሆነ በኃይልም ቢሆን በቤጂንግ ሥር እንደምትሆን ታምናለች።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ከታይዋን ጋር “መዋሃድ መሳካት አለበት” ብለዋል።