አሜሪካ የፍልስጤም ፕሬዚዳንት በኒው ዮርክ የተመድ ጉባኤ እንዳይገኙ አገደች

አሜሪካ የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ እና 80 ባለስልጣናትን ቪዛ በመሰረዝ በሚቀጥለው ወር በኒውዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳይገኙ መከልከላቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

አሜሪካ የባለስልጣናቱን ቪዛ የሰረዘችው ፈረንሳይና ካናዳን ጨምሮ አንዳንድ አገራት ለፍልስጤም አገርነት በይፋ እውቅና በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንሰጣለን ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የፍልስጤም ባለስልጣናትን የሰላሙን ጥረት በማናጋት እንዲሁም "የአንድ ወገን የፍልስጤም ዕውቅናን በመሻት" ከሰዋቸዋል።

እስራኤል ይህንን የባለስልጣናቱን ቪዛ የመሰረዝ ውሳኔ በበጎ እንደምትቀበለው አስታውቃለች።

አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መገኘት ለሚፈልጉ የሁሉም አገራት ባለስልጣናት ጉዞን ማመቻቸት የሚጠበቅባት ዋነኛ ተግባር ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ውሳኔው ያልተለመደ ነው ተብሏል።

በዚህ ጉባኤ ላይ ፍልስጤም በአገርነት ዕውቅና እንዲሰጣት ፈረንሳይ ዓለም አቀፍ ጥረቶችን እየመራች ትገኛለች።

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ይህንን በጽኑ ተቃውሞታል።

በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ መንሱር ፕሬዚዳንት አባስ በኒው ዮርክ በሚካሄደው የመሪዎች ስብሰባ እንደሚገኙ ቀደም ብለው ተናግረው ነበር።

ነገር ግን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት እና የፍልስጤም አስተዳደር ባለስልጣናትን ቪዛዎች ለመሰረዝ እና ለመከለልከል በመወሰን ፕሬዚዳንት አባስ እና ሌሎች 80 የሚሆኑ ባለስልጣናትን ማገዱን አስታውቋል።

ማርክ ሩቢዮ በኒውዮርከ የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ተወካዮች በአሜሪካ የተባበሩትን መንግሥታት ሥራዎችን በሚቆጣጠረው ሰነድ መሰረት በጉባኤው ላይ መገኘት ይችላሉ ብለዋል።

ይህ ሰነድ "በአገራቱ መንግሥታት እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ምንም ይሁን ምን" የውጭ አገር ባለስልጣናት በተመድ ዋና ቢሮ ኒው ዮርክ ለመገኘት አሜሪካ ማደናቀፍ እንደማይገባት የሚገልጽ ነው።

የፕሬዚዳንት አባስ ቢሮ ይህ የቪዛ ውሳኔ እንዳስገረመው ገልጾ "የፍልስጤም ግዛት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታዛቢ አባል ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የአለም አቀፍ ህግ እና የተቋሙን ዋና መስሪያ ቤት ስምምነት የሚጻረር ነው" ሲል ገልጿል።

አሜሪካ ይህንን ውሳኔ እንድትቀለብስም አሳስቧል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውሳኔውን በመልካም ሁኔታ መቀበላቸውን አስታውቀዋል።

ሐማስ የጋዛ ሰርጥን ለዓመታት ሲያስተዳድር የቆየ ሲሆን ተቀናቃኙ ፋታህ እስራኤል በኃይል ወራው በምትገኘው ዌስት ባንክ የተወሰኑ ግዛቶችን ያስተዳድራል።

በፕሬዚዳንት አባስ የሚመራው የፍልስጤም አስተዳደር እስራኤል ከምታደርገው ከአይሁድ የሰፈራ መስፋፋት ጋር እየተጋፈጠ ይገኛል።

አባስ በተጨማሪም ፍልስጤማውያኑን በዓለም አቀፍ መድረክ የሚወክለው የፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት (ፒኤልኦ) ድርጅት ኃላፊ ናቸው።

ፒኤልኦ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአውሮፓውያኑ 1974 ጀምሮ የታዛቢነት ሥፍራ ተሰጥቶታል። በጉባኤዎች ላይ መሳተፍ ቢችልም በውሳኔዎች ላይ ድምጽ አይሰጥም።

በአሁኑ ወቅት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል 140ዎቹ ፍልስጤምን በአገርነት ዕውቅና ይሰጧታል።

ከእነዚህም መካከል ስፔንና አየርላንድን ጨምሮ ጥቂት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ይገኙበታል።

እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሰረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን ይህንንም "ናቅባ" (ትልቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኛዎቹ በጋዛ ሰፍረዋል።

በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።

3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ ሶሪያ እና ሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ እየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።

አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።

እስራኤል ይህንን አትቀበልም።

በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።