ከሊቢያ የተነሳ የስደተኞች ጀልባ ተገልብጦ 53 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 55 ተሳፋሪዎችን የያዘ የፕላስቲን ጀልባ በሊቢያ ባሕር ዳርቻ ተገልብጦ ከሁለቱ በቀር ሁሉም ስደተኞች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ተቋም አስታወቀ።
የሊቢያ ባለሥልጣናት ከአደጋው በሕይወት የተረፉት ሁለት ናይጄሪያውያን ሴቶች መታደጋቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ሰኞ ዕለት አስታውቋል።
እንደ ተቋሙ ገለጻ አርብ ዕለት አደጋ ያጋጠመው ጀልባ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ፍልሰተኞችን እና ስደተኞችን ጭኖ ነበር።
አደጋው የደረሰው ጀልባው ሰል ዛዊያ ከተባለው የሰሜን ምዕራብ ሊቢያ ከተማ ከተነሳ ከስድስት ሰዓታት በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።
በሕይወት የተረፉት ስደተኞች ለአይኦኤም እንደተናገሩት፤ ጀልባው ከአል ዛዊያ ተስቶ ጉዞውን የጀመረው በአካባቢው የሰዓት አቆጣጠር ሌሊት ስድስት ሰዓት ገደማ ነው። ጉዞውን ከጀመረ ከጥቂት ሰዓታት በኋላም ተገልብጧል።
አርብ ዕለት የደረሰው አደጋ ለምን እስከ ሰኞ ሳይሰማ እንደቀረ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ከአደጋው ከተረፉት ሴቶች አንዷ አብሯት ሲጓዝ የነበረው ባለቤቷ እንደሞተ ተናግራለች። ሌላኛዋ ደግሞ ሁለት ልጇቿ ሕይወታቸው ማለፉን እንደገለጸች የአይኦኤም መረጃ አሳይቷል።
የዓለም አቀፉ ስደተኞች ተቋም ቡድኖች ለሁለቱ ሴቶች አስቸኳይ የሕክምና ድጋፍ እያቀረቡ እንደሆነ ተገልጿል።
የተቋሙ መረጃ እንደሚያመለክተው የአውሮፓውያኑ 2026 ከገባ አንስቶ ከሊቢያ ተነስተው በሜዲቲራኒያን ባሕር ለማቋረጥ የሞከሩ 500 ገደማ ስደተኞች ሕይወታቸው አልፏል አልያም ጠፍተዋል።
ከፍተኛ የክረምት የአየር ሁኔታ በታየበት ጥር ወር በመካከለኛው ሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ባጋጠሙ ተከታታይ "ትኩረት ያላገኙ" የመርከብ አደጋዎች ምክንያት ቢያንስ 375 ስደተኞች መሞታቸው ወይም መጥፋታቸው ሪፖርት ተደርጓል።
ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ግን ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ። እንዲህ ዓይነት ሞት እና አደጋዎች በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ቢሆንም ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባሕር ለማቋረጥ የሚያደርጉት ጥረት አልቆመም።
በአውሮፓውያኑ 2011 የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ከተገደሉ ጊዜ አንስቶ ሊቢያ ወደ አውሮፓ መድረስ የሚፈልጉ የበርካታ የአፍሪካ አገራት ስደተኞች ዋነኛ መተላለፊያ ሆናለች።
ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ የሚያሳልፉት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ በስፋት ተሰንዷል።
ሊቢያ ውስጥ ስደተኞች ስቅይት፣ ሕገ ወጥ ዝውውር፣ የግዳጅ ሠራተኝነት፣ የገንዘብ ብዝበዛ እና ሌሎች ግፎችም በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት እንደሚፈጸሙባቸው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት እንደሚናገረው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረቦችን የሚያንቀሳቅሱ አካላት ስደተኞች በተጨናነቁ እና በባሕር ላይ ለመጓዝ በማይሆኑ ጀልባዎች እንዲጓዙ ያደርጋሉ። ይህ ሁኔታም የስደተኞች የሞት መጠን እንዲጨምር አንድ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
የሰዎች ዝውውር መረቦችን ለመበጠስ እንዲሁም በባሕር ላይ የሚደረጉ ጉዞዎችን በመቀነስ ለስደተኞች ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ሕጋዊ መተላለፊያ ለመፍጠር ጠንካራ ዓለም አቀፍ ትብብር ሊኖር እንደሚገባ ተቋሙ አሳስቧል።
ብዙውን ጊዜ መርከቦች በሚገለበጡበት ወቅት አዘዋዋሪዎች ስለደረሰው ጉዳት ሪፖርት አያደርጉም። ጀልባ ተገልብጦ የሚሞቱ ስደተኞች እንዲሁ ደብዛቸው ይጠፋል፤ ቤተሰቦቻቸውም ምን እንደደረሰባቸው የሚያውቁበትም ዕድል የለም።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ስፔን፣ ኖርዌይ እና ሴራሊዮንን ጨምሮ በርካታ አገራት ሊቢያ የስደተኞች ማጎሪያ ካምፖችን እንድትዝገባ ጥሪ አቅርበዋል። ስደተኞች በእነዚህ ማጎሪያዎች ውስጥ ስቅይት፣ ግፍ እና ግድያ እንደሚፈጸምባቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ይናገራሉ።















