ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሚያንማር በተከሰተው ርዕደ መሬት ቢያንስ 1002 ሰዎች ሞቱ
በሚያንማር በተከሰተው ርዕደ መሬት እስካሁን ድረስ ብቻ ቢያንስ 1002 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች 2,376 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
30 ሰዎች ደግሞ መጥፋታቸው ተገልጿል።
ትናንት በ7.7 ማግኒትዩድ የተለካ ርዕደ መሬት የተከሰተ ሲሆን ከሚያንማር አልፎ በአጎራባች አገራትም ንዝረቱ ተሰምቷል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሰዎችን ሕይወት ለማዳን እየተተረባረቡ ቢሆንም የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው።
"በእጃችን እየቆፈርን ሰዎች ለማዳን እየሞከርን ነው" ሲል አንድ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ቡድን ለቢቢሲ ገልጿል።
በባንኮክ በግንባታ ላይ በነበረ ሕንጻ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ 100 ሠራተኞች እስካሁል አልተገኙም። ከመካከላቸው ስድስቱ መሞታቸው ተገልጿል።
የሚያንማር ወታደራዊ መንግሥት ዓለም አቀፍ እርዳታ ጠይቋል።
ሚያንማር ራሷን አግልላ የምትኖር አገር ብትሆንም የርዕደ መሬቱ ስፋት ወታደራዊ መንግሥቱ ድጋፍ እንዲጠይቅ አስገድዶታል።
ወታደራዊ መንግሥቱ በሰጠው መረጃ መሠረት 694 ሰዎች የሞቱት ማንዳላይ በተባለው ከተማ ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ያለው የተጎጂዎች ቁጥር 1,002 ደርሷል።
ማንዳላይ የሚያንማር ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ስትሆን በርዕደ መሬቱ ክፉኛም ተጎድታለች።
ሕንድ ለሚያንማር እርዳታ ከላኩ አገራት አንዷ ናት። በሚያንማር ለሚገኙ የርዕደ መሬት ተጎጂዎች ድጋፍ መስጫ ማዕከላት መገልገያዎችን አድርሳለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲ "ድጋፍ ለመስጠት በተጠንቀቅ እየተጠባበቅን ነው" ብለዋል።
የ45 ዓመት ባለቤቷን ለማግኘት እየሞከረች ያለችው ናርሞል ከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ መሆኗን ትናገራለች።
እስካሁን ድረስ ካልተገኙ የግንባታ ባለሙያዎች አንዱ ባለቤቷ ነው።
ናርሞል የእምባ ሳግ እየተናነቃት ባለቤቷ ያለበትን ማወቅ አለመቻሉት ትገልጻለች።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተጎጂዎችን በሕይወት ለማግኘት ሙከራቸውን ቀጥለዋል።
በማንዳሊ የሚኖር አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ በርሚዝ እንደተናገረው ድንገት ርዕደ መሬቱ ሲነሳ መሬቱ በአንድ ጊዜ ተናውጧል።
ወደ 10 ሰከንድ መሬቱ ከተንቀጠቀጠ በኋላ መላው ቤቱ መናዱን ገልጿል።
"ሙሉ ቤታችን እያየሁት ተናደ። ላዬ ላይ ሊወድቅ ስል ለማምለጥ ስሞክር ተደናቅፌ ወደቅኩ። መተንፈስ አልቻልኩም። በጩኸት ሰዎች እንዲረዱኝ ተጣራሁ። አባቴና አጎቴ ደረሱልኝ። ከሌሎች ስድስት ሰዎች ጋር ተባብረው ከቤቱ አወጡኝ" ይላል።
የመጀመሪያውን ዙር ርዕደ መሬት ተከትሎ ሰዎች ከቤታቸው ለመውጣት ሲሞክሩ በድጋሚ ርዕደ መሬቱ ተከስቷል።
የማንዳሊው ነዋሪ ቢተርፍም አንድ አክስቱ ሞታለች፤ ሌላዋ አክስቱ ደግሞ ተጎድታ ሆስፒታል ገብታለች።
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቪስ እንዳለው ርዕደ መሬቱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ሊገድል ይችላል።
ይህ ግምት የተቀመጠው ከርዕደ መሬቱ የንዝረት መጠን አንጻር ነው። ከርዕደ መሬት በኋላ ሊነሱ የሚችሉ እንደ መሬት መንሸራተት ያሉ አደጋዎችን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ነው ግምቱን ያስቀመጠው።
ቻይና 37 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ወደ ሚያንማር ልካለች። ሌላ ርዕደ መሬት ሊከሰት እንደሆነ የሚጠቁም መሣሪያ፣ ሰው አልባ አውሮፕላን እንዲሁም የሳተላይት መሣሪያዎችን እየተጠቀሙ ነው።
በቻይና የሚገኘው ዩናን ግዛት ውስጥ የርዕደ መሬቱ ንዝረት ይሰማ እንደነበር ተገልጿል።